አባይ ሚዲያ መጋቢት 14፤2012

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አቅም ለሌላቸው መንገደኞች ወጪያቸውን እሸፍናለሁ አለ ከውጪ አገራት መጥተው ለለይቶ ማቆያ የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ መሸፍን ለማይችሉ ኢትዮጵያዊያን የአዲስ አበባ መስተዳደር ወጪያቸውን እንደሚሸፍን አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ወደ ለይቶ ማቆያ ለሚገቡ ሰዎች የሚያስፈልገውን ወጪ እንደሚጸፈንላቸው በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል ምክትል ከንቲባው እንዳሉት “ለቆይታ ጊዜው ወጪያቸውን መሸፈን ለማይችሉ ዜጎቻችን ሙሉ ወጪያቸውን እኛ እንሸፍናለን።”

በተጨማሪም ከንቲባው በተለያየ መንገድና ለተለያዩ ጉዳዮች ከኢትዮጵያ ውጭ የነበሩ ዜጎች “ወደ ኅብረተሰቡ ከመቀላቀላቸው በፊት ለሁለት ሳምንታት ተለይተው የሚቆዩባቸውን ስፍራዎች” መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል ባለፈው አርብ የኮሮናቫይረስን ለመካላከል ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት ከዛሬ ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሰዎች በእራሳቸው ወጪ ለለይቶ ማቆያነት በተመረጡ ቦታዎች እንዲቆዩ እንደሚያደርግ አሳውቆ ነበር በዚህም መሰረት ይህ ውሳኔ ወደ ኢትዮጵያ በሚገቡ ሰዎች ላይ የ14 ቀናት ወደ ለይቶ ማቆያ የማስገባቱ ሥራ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ እየሆነ ነው።

ቀደም ሲል የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዳሳወቀው ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሰዎች ለለይቶ ማቆያነት በተለዩት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለቤትንት በሚተዳደረው በስካይ ላይት እና የመንግሥት ንብረት በሆነው ጊዮን ሆቴሎች ውስጥ ወጪያቸውን እራሳቸው ሸፍነው ይቆያሉ።

ከእነዚህ ውጪ ያሉ ዲፕሎማቶች ደግሞ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ የየአገሮቻቸው በኤምባሲዎች ውስጥ ለሁለት ሳምንታት ተለይተው እንደሚቆዩና ክትትል እንደሚደረግባቸው ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት የኮሮና ስርጭትን ለመቆጣጠር የተሳፋሪውን ቁጥር 50 በመቶ ቀንሷል ተሳፋሪዎች እጅግ የሚጨናነቁበት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት አገልግሎት ከዛሬ ጀምሮ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር የተሳፋሪውን ቁጥር 50 በመቶ ቀንሶ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑ ታውቋል።

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ፥ እርምጃው የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ያለመ መሆኑን አስታውቀዋል አያይዘውም ህብረተሰቡ የትራንስፖርት ጥግግት መጠንን በመቀነስ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል።

ይህ በአንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ከተያዙ 11 ሰዎች መካከል ሁለቱ ጃፓናዊያን  ወደ አገራቸው መሸኘታቸውን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ አስታውቀዋል።