አባይ ሚዲያ መጋቢት 14፤2012

በጌዲዮ ከ 1 ሺህ በላይ የብልፅግና ፓርቲ አባላት ለ5 ቀን የሚቆይ ስብሰባ ዛሬ ይጀምራሉ በጌዲዮ ዞን በሚገኙ 12 ወረዳዎች ስር ከሚገኙ 164 ቀበሌዎች የተወጣጡ 1640 ሰዎች በየወረዳቸው ከዛሬ መጋቢት 14/ 2012 ጀምሮ ለአምስት ቀናት የሚቆይ የብልፅግና ፓርቲ የበታች አመራር ስልጠና እንደሚጀምሩ ከስፍራው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ይህ ስብሰባ በክልሉ ባሉ የተለያዩ ዞኖችም እንደሚካሄድ ያመለከተቱት ነዋሪዎች ነገር ግን ከመንግስት እውቅና ውጪ ፓርቲው ያደርገዋል ብለው አንደማያምኑ ተናግረዋል።

‹‹ክልሉ በኮማንድ ፖስት ስር ያለ ሲሆን ማንኛውም አይነት ስብሰባ የሚመለከተው የፌደራል የፀጥታ ሃይል ነው። ስለዚህ የፌደራል መንግስቱ አውቆ እና አምኖበት የፈቀደው ነው ብለን ነው የምናምነው›› ሲሉ በዞኑ ያሉ መካከለኛ አመራር ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ ባወጣችው ዘገባ ደግሞ በሶማሌ ክልል የገዢው ፓርቲ ስብሰባዎች ባይኖሩም ሌሎች በርካታ ስብሰባዎች ግን እንደቀጠሉ ናቸው።

ኢትዮጵያ ውስጥ መግባቱ በተረጋገጠው የአለም ስጋት የሆነው ኮሮና ቫይረስ ምክናየት የኢትዮጵያ መንግስት ምንም ዓይነት ስብሰባ መከልከሉ የሚታወቅ ነው፡፡

ነገር ግን ብልፅግና ፓርቲ  ከስብሰባ አልፎ ካድሬዎቹን እያሰለጠነ ነው በሚል ወቀሳዎች እየቀረበቡትና ለቫይረሱ ስርጭት ምክናየት እንዳይሆን ስጋታቸውን የሚገለጹ ጥቂቶች አይደሉም፡፡

የብልፅግና ፓርቲ የውጪ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አወሉ አብዲ በበኩላቸው ውይይቱ የካድሬዎች ስልጠና ሳይሆን የህዝብ ጥያቄን የሚመለከትና በየአመቱ የሚሰጥ የመንግስት አመራሮች ስልጠና ነው ያሉ ሲሆን በርግጥ ከቫይረሱ መምጣት በፊት ይዟቸው የነበሩ አጀንዳዎች ተቀይረዋል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ሃላፊው እንደሚሉት በብልጽግና ደረጃ የታሰቡ የመካካለኛና የዝቅተኛ አመራሮች ስልጠናዎች በአማራና በድሬዳዋ ከተጠናቀቁ ቆይተዋል ነገር ግን የሌሎች አካባቢዎችን የዝቅተኛ አመራሮች ስልጠናዎች በዋነኝነት ዋና አጀንዳቸው ስለኮኖና ቫይረስ ስርጭት ግንዛቤ ማስጨበጥ ነው፡፡

በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ስጋት ስለፈጠረው  ገዳይ በሽታ ለገጠሩ ማህበረሰብ  ግንዛቤ ለመፍጠር ታች ላሉ የቀበሌ አመራሮች የተሰጠው ስልጠና ለህዝቡ እንዲያደርሱ ያለመ ነው የሚሉት አቶ አወሉ ብልጽግና ቀድሞውኑ በፕሮግራም ደረጃ ያሰባቸው ስልጠናዎች ሌላ ቢሆኑም ባለው ወቅታዊ ችግር ምክናየት ስብሰባው ስለ ኮሮና መረጃ መስጠቱ ላይ ሆኗል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አቶ አወሉ አክለውም በሽታው ገባ ብሎ እጅን አጣጥፎ ከመቀመጥ ባለው ጊዜ መፍትሄ ለመፈለግ ያክል ስልጠናዎቹ ተሰጥተዋል፤ አመራሮቹም በየቀበሌያቸው ማህበረሰቡ ቅድመ ጥንቃቄዎችን እንዲወስድ ይሰራሉ ብለዋል፡፡