አባይ ሚዲያ መጋቢት 15፤2012

ኢዜማ በኮሮና ቫይረስ ምክናየት የሚፈጠሩ ሀገራዊ ተጽዕኖዎች ለሚመለከታቸው አካላት መረጃ መስጠት እንደሚገባ አሳሳበ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ ኢዜማ አለም አቀፍ ስጋት የሆነውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሚመለከት በላከው መግለጫ በሽታው ይዞት የሚመጣው ተጽዕኖ ታውቆ አስፈላጊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ጠይቋል፡፡

ኢዜማ በመጪው ነሐሴ 23 2012 ይካሄዳል ተብሎ ቀን ስለተቆረጠለት ሀገራዊ ምርጫ እንዳለው  መንግሥት ወረርሺኙን ለመግታት ለአጭር ጊዜ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች በምርጫ ጊዜ ሰሌዳው ላይ ከአሁኑ ተጽዕኖ እያሳደሩ መሆኑን ተገንዝቧል፡፡

ፓርቲው ከየትኛውም የፖለቲካ እቅስቃሴ በፊት የዜጎች ደህንነት ቅድሚያ ማግኘት የሚገባው ጉዳይ በመሆኑ፣ ከሰኞ መጋቢት 7 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የታቀዱ ማንኛውም ሕዝባዊ ስብሰባዎችንም ሆነ እጅግ አስፈላጊ ያልሆኑ የፓርቲያችን ስብሰባዎችን በሙሉ ላልተወሰነ ጊዜ ማቆሙን አውስቷል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ወረርሽኙ እዳይስፋፋ መንግሥት የወሰናቸው ውሳኔዎች እና ወደፊትም የሚወሰኑ ውሳኔዎች የምርጫው የጊዜ ሰሌዳ ላይ የሚፈጥረውን ተጽዕኖ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት በግልጽ እያሳወቀ እንዲቀጥል እና ምርጫ በሚካሄድበት ቀንም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ ማንኛውም ማሻሻያዎች ሁሉንም ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ውይይት እያደረገ እንዲወስን ጠይቋል፡፡

ኢዜማ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ጸጥታን ከማስከበር አንጻር የስልክ እና የኢንተርኔት ግንኙነት ከተቋረጠ ወራት መቆጠሩን አስታውሶ በዚህ ወሳኝ ወቅት መስተካከል እንዳለበትና ዜጎች እራሳቸውን ለመከላከል ስለቫይረሱ ስርጭት ትክክለኛ እና ጊዜውን የጠበቀ መረጃ እንዲደርሳቸው አስፈላጊ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የዚህ ግንኙነት አለመኖር በአካባቢው ያለውን የስርጭት ሁኔታ ለመከታተል እና አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ለመንግሥት ሊደርሱት የሚገቡ መረጃዎችን ለመሰብሰብም አዳጋች ያደርገዋል ሲል ያክላል፡፡

ይህን ከግምት በማስገባት መንግሥት በአካባቢው የተቋረጠውን የስልክ እና የበይነ መረብ ግንኙነት ወደሥራ እዲመለስ እንዲያደርግ ያሳሰበው ኢዜማ ከዚህ ጋር ተያይዞ ለሚመጣ የጸጥታ እና ደኅንነት ስጋት አማራጭ መፍትሄዎችን በፍጥነት እንዲያዘጋጅ አመልክቷል፡፡

መግለጫው አክሎም እስካሁን ተቋርጦ በነበረው ግንኙነት ምክንያት የተፈጠረውን የመረጃ ክፍተት ለማካካስ በአካባቢው ከሚሰራጩ የመገናኛ ብዙሃን ጋር በመሆን ሰፊ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እንዲሠራ ለመንግስት ጥያቄ አቅርቧል፡፡