አባይ ሚዲያ መጋቢት 15፤2012

ከቀናት በፊት በጎንደር ከተማና በዳባት አካባቢ በፋኖ አደረጃጀት በተፈጠረው ውዝግብ በተከፈተ ተኩስ የሞትና የመቁሰል አደጋ መድረሱን ተከትሎ የጎንደር ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ምክር ቤት መግለጫ ሰጥቷል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ እውነተኛው የፋኖ ንቅናቄ የመላው አማራ ክልል ሕዝቦች የለውጥ ንቅናቄ መጠሪያ ሁኖ ለለውጡ ያበረከተው አስተዋጽኦ ማንም ደፍጥጦት የሚያልፍ ጉዳይ አይደለም ሲል ያትታል፡፡

ነገር ግን አሁን በተለይም በከተማዋ እየተፈፀመ ያለው ጉዳይ ከዚህ የተለየ ነው ያለው መግለጫው ከዋናው ፋኖ ዓላማ ውጭ በሕገ ወጥ መንገድ በቡድን ተደራጅቶ እየተንቀሳቀሰ ያለው ቡድን በርካታ ሕገ ወጥ ተግባራትን አከናውኗል ሲል ይከሳል፡፡

ቡድኑ ከሚፈፅማቸው ሕገ ወጥ ተግባራት መካከል ታጥቆና ተደራጅቶ በከተማው በመንቀሳቀስ ያለምንም ከልካይ ኬላ ጥሶ ከከተማ መውጣት፤ ሰው ማገት፤ ግድያ መፈጸም፤ ዘር ቆጥሮ የግለሰብ ቤት ነጥቆ ካምፕ ማድረግ፤ ከባለሀብት በግዴታ ገንዘብ መሰብሰብ ፤ በፖሊስ እጅ ያለ ተጠርጣሪ ወንጀለኛ እስር ቤት ጥሶ ገብቶ ማስፈታትና የፓርቲ ቢሮዎችን በመክበብ ማስፈራራትና አመራር ለመግደል ማቀድ እንደሚገኙበት ተጠቅሷል፡፡

ይህ ሁሉ ችግር እየተፈጠረ መሆኑን እያወቀ የክልሉ መንግሥትና የከተማ አስተዳደሩ ይህንን ኃይል በሠለጠነና በሠላማዊ መንገድ ያለ ደም መፋሰስ ከዚህ ሕገ ወጥ ድርጊቱ ታቅቦ የመንግሥት ተገዳዳሪ ኃይል ሳይሆን ወደ መደበኛ ሕይወቱ እንዲመለስ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን አስቀምጦ ወደ ተግባር ለመግባት ዝግጅት እያደረገ ባለበት ወቅት ጥቃት መፈፀሙንም የከተማ አስተዳደሩ ይገልጻል፡፡

በወቅቱ የተፈጠረውን ብጥብጥ በመግለጫው ያስታወሰው ምክር ቤቱ ችግሩ በዚህ ብቻ አላበቃም፤ በሚቀጥሉት ቀናትም ሕገ ወጥ ሰልፍና ሕገ ወጥ የሥራ ማቆም አድማ ለማካሄድ ከመሀል አገር አዲስ አበባ ድረስ የተላኩ በተሽከርካሪ የታገዘ የአድማ ወረቀት የመበተንና በሕገ ወጥ መንገድ የተደራጀው ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በመቃወም መንግሥትን እየተገዳደረ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ሌሎች ተላላኪ ኃይሎች በርካታ ጥረት አድርገዋል ብሏል፡፡

በቀጣይም ማንኛውም ቡድን ወይም ግለሰብ በከተማው ውስጥ ታጥቆ እንቅስቃሴ ማድረግ የተከለከለ ሲሆን ይህንን የክልሉ መንግሥት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ መመሪያ የጣሰ የያዘውን የጦር መሣሪያ አውርዶ በሕግ የሚጠየቅ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው ብሏል፡፡

በተጨማሪም በሕገ ወጥ መንገድ የተደራጀው ነገር ግን አሁን የተበተነው ቡድን በሠላም እጁን ለመንግሥት እስከ መጋቢት 20/2012 እንዲሠጥ፤ ይህንን አልፈፅምም ካለ ቡድኑን የመንግሥት የፀጥታ ኃይል ለሕግ በማቅረብ የሕግ የበላይነትን ያረጋግጣል ብሏል፡፡