አባይ ሚዲያ መጋቢት 15፤2012

በኮሮና ቫይረስ የተያዘ አንድ ተጨማሪ ሰው በመገኘቱ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 12 መድረሱን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል የ34 ዓመት ኢትዮጵያዊው ታማሚ መጋቢት 10 ቀን 2012 ዓ.ም ከዱባይ የገባ ሲሆን መጋቢት 13 ቀን 2012 ዓ.ም ባደረገው ምርመራ በቫይረሱ መያዙ ተረጋግጧል፡፡

ከታማሚው ጋር ግንኙነት የነበራቸው 15 ሰዎችም ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኙ ኢንስቲትዩቱ ገልጿል በተያያዘ ዜና የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ዛሬ ከዱባይ የመጡ ኢትዮጵያውያንን የከተማ አስተዳደሩ መቀበሉን ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያውያኑ በአስተዳደሩ ወደተዘጋጀላቸው ስፍራ ለሁለት ሳምንታት እንደሚቆዩም ምክትል ከንቲባው አስታውቀዋል፡፡

ምክትል ከንቲባው ይህን ይበሉ እንጂ ከዱባይ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ኢትዮጵያውያን ለአባይ ሚዲያ እንደተናገሩት ከሆነ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በተላለፈው መመሪያ መሰረት በሆቴል ለመቆየት እስከ 50 ዶላር እየተጠየቅን በመሆኑ እንግልት እየደረሰብን ነው ብለዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በቦሌ ዓለም ዐቀፍ አየር ማረፊያ ለኮሮና ቫይረስ የሚደረገው ምርመራ አጥጋቢ አለመሆኑን በአየር መንገዱ አገልግሎት የሚያገኙ ተጓዦች አየገለፁ ነው።

ሥማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ከደቡብ አፍሪካ ወደ ኢትዮጵያ ከቀናት በፊት የመጡ ተጓዦች  እንደተናገሩት፣ በአየር መንገዱ የሙቀት ምርመራ ለማከናወን ረዥም ሰልፍ ሲጠባበቁ ከቆዩ በኋላ በአየር መንገድ የቫይረሱን ምርመራ የሚያከናውኑ ባለሙያዎች የተሰለፉትን ሰዎች የመጡበትን አገር እየጠየቁ እንዲያልፉ ሲያደርጉ ተመልክተዋል።

አክለውም ቫይረሱ በወቅቱ ከደቡብ አፍሪካም ጭምር መስፋፋት የጀመረበት ወቅት እንደነበር የጠቆሙ ሲሆን፣ በባለሙያዎቹ ድርጊት መደናገጥ ውስጥ ገብተው እንደነበር ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከአንድ ሳምንት በፊት ምርመራው በትኩረት ሲሰጥ የነበረው ከ8 አገራት ለሚመጡ ተጓዦች ብቻ እንደነበር የሚገልፁት የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮሮና ቫይረስ ቅድመ ዝግጅት እና ምላሽ አስተባባሪ ዘውዱ አሰፋ ናቸው።

ከቫይረሱ በቻይና መከሰት በኋላም ቻይና ጨምሮ ቫይረሱ ከተስፋፋባቻው ጣሊያን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ኢራን፣ ጃፓን ጀርመን እና ዱባይ የሚመጡ ተጓዦች ላይ ትኩረት ተደርጎ ምርመራ ሲደረግ እንደነበር ዘውዱ ገልፀዋል።

ከእነዚህ አገራት የሚመጡ ተጓዦችን ፓስፖርት በመመልከት ልዩ ትኩረት ተደርጎባቸው የሰውነት ሙቀት ምርመራ ሲደረግባቸው ቆይቷል ያሉት ዘውዱ፣ ከሌሎች አገራት የሚመጡ ተጓዦችን ግን በጅምላ ማስተር ቴርሞ ስካነር በተሰኘ መሣሪያ የሙቀት ልየታ ሲደረግባቸው ቆይቷል ብለዋል።

አሁን የሚነሱት ጥያቄዎች ተጓዦች ማስተር ቴርሞ ስካነር የሚደረገውን የሰውነት ሙቀት ልየታ ልብ ባለማለታቸው የመጣ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።