አባይ ሚዲያ መጋቢት 16፤2012

የታላቁ ህዳሴ ግድብ አጠቃላይ የግንባታ ሒደት 72 በመቶ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ  አስታወቁ፡፡

በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎቹ ከ42.3 በመቶ በላይ የደረሱት የህዳሴው ግድብ፣ እንደ አዲስ እየተገነባ የሚገኘውና በርካታ ችግሮች አጋጥመውት የነበረው የሲቪል ስትራክቸር የግንባታ ሒደትም ከ20 በመቶ በላይ አፈጻጸም ማስመዝገቡን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ግንባታው እየተፋጠነ ስለሆነ በአሁኑ ወቅት 4.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ማከማቸት የሚችልበት አቅም ላይ እንዲደርስ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ውኃው በክረምቱ ወራት በግድቡ ውስጥ ተጠራቅሞ፣ ሁለት የኃይል ማመንጫ ተርባይኖችን የመሞከርና የሙከራ ኃይል ማምረት እንደሚጀመር አስረድተዋል ይህም በመጪው ዓመት የካቲትና መጋቢት ወራት ውስጥ እንዲካሄድ መታቀዱን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ‹‹አሁን የምንገኝበት አፈጻጸም በዚህ ደረጃ ላይ ይገኛል፣ ግንባታውም በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል፤›› ሲሉም አስታውቀዋል፡፡

ሁለቱ የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች ከ700 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጩ መሆናቸውን፣ ይህም ቅድመ ማመንጨት ሥራን መሠረት ያደረገ እንደሆነ፣ እያንዳንዱ የኃይል ማመንጫ ተርባይን 375 ሜዋ ጋት በጠቅላላው 750 ሜጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት የሚችሉበት አቅም እንዳላቸው ከሚኒስትሩ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ይሁን እንጂ ይህን ያህል መጠን ያለው ኃይል ለማምረት የተከማቸ ውኃና የልቀት መጠን ላይ የሚመሠረት ቢሆንም፣ በክረምት ወራት በግድቡ ውስጥ የሚከማቸው ውኃ ከ565 ሜትር ከፍታ ላይ ሊደርስ እንደሚችል በመታሰቡ፣ ቅድመ ማመንጨት ሥራውን ለማከናወን የሚያስችለው የውኃ መጠን ሊከማች እንደሚችል ይጠበቃል ሲሉም አክለዋል፡፡

የህዳሴ ግድብ በማንኛውም ትልልቅ የግድብ ግንባታዎች ላይ ሊያጋጥም የሚችል ፈታኝ ሁኔታ ቢያጋጥመውም፣ መሠረቱን ለማውጣት የፈጀው ጊዜ የግድቡን የውኃ አቅጣጫ ማስቀየሪያ ከልቨርት ለመገንባት የሚጠበቀውን ጊዜ እንዳጓተተው፣ ከዚያም ወዲህ የኃይድሮሊክና የስቲል ስትራክቸር ግንባታውና የተርባይን ገጠማ ሥራዎች በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ እንዳለፉ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የስቲል ስትራክቸር ግንባታ እንዲያካሂዱ ሥራው በተሰጣቸው ተቋራጮች ሥራው ሲጓተት ቢቆይም፣ በአሁኑ ወቅት በሚታየው አጠቃላይ የሥራ ሒደት ግድቡ በፍጥነት እየተገነባ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የግድቡ ግንባታና አጠቃላይ የቴክኒክ ጉዳዮች፣ እንዲሁም መሠረታዊ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ዕቅዶችና ዝርዝር ሥራዎች ከመነሻው ፕሮጀክቱን ስትቃወም ለቆየችው ግብፅም ሆነ ለሌሎች የተፋሰሱ አገሮች መረጃዎች በግልጽ ሲቀርቡላቸው ቢቆዩም፣ በግብፅ በኩል ግን በግድቡ ግንባታ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞና ቅስቀሳዎች ሲደረጉበት መቆየቱ ይታወሳል፡፡