አባይ ሚዲያ መጋቢት 16፤2012

አለም አቀፍ ስጋት በሆነው የኮሮና ቫይረስ ምክናየት በመላው የአለም ሀገራት የተለያዩ የቅድመ መከላከልና የመቆጣጠር ሂደት እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰአታት የኮሮና ቫይረስ ምርመራ የተደረገላቸው 106 ሰዎች ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዛሬ በሰጠው መግለጫ አረጋግጧል፡፡

እስካሁን በሁሉም መግቢያ በሮች 668 ሺህ ሰዎች ወደ ሃገር ውስጥ መግባታቸውን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ ተናግረዋል በሌላ በኩል 20 ሰዎች የበሽታው ምልክት ታይቶባቸው በለይቶ ማቆያ ውስጥ ሆነው የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤታቸውን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስተሩ ያሳለፉቸውን ውሳኔዎች ተከትሎ በየደረጃው ያለውን ተፈጻሚነት በሚኒስትሮች ደረጃ የተቋቋመው ከሚቴ በበላይነት በመከታተል ላይ ይገኛል ወደ ሀገር ውስጥ መግቢያ ጣቢያዎች እየተደረገ የሚገኘው ምርመራም የተጠናከረ ሲሆን 668 ሺህ 476 ሰዎች በሙቀት መለያ ተደርጎላቸዋል።

በሙቀት መለያ ካለፉት 12 ሺህ 245 ያህሉ በሽታውን ሪፖርት ካደረጉ ሃገራት የመጡ ናቸው ተብሏል በኢትዮጵያ የኮሮና ወረርሽኝን ለመግታት በመንግስት ደረጃ ከተወሰዱ እርምጃዎች ዛሬ ላይ ይፋ የተደረገው ከ4 ሺህ በላይ እስረኞች እንዲፈቱ መሆኑ ነው የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በፌደራል ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ለ4011 የሕግ ታራሚዎች በይቅርታ እንደሚፈቱም ጠቅላይ ዐቃቢተ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አስታውቀዋል።

በይቅርታው የተካተቱ ታራሚዎች እስከ 3 ዓመት የሚደርስ ቀላል እስራት የተፈረደባቸው ታራሚዎች፤በማረሚያ ቤት ሆነው አንድ ዓመት የአመክሮ ጊዜ የሚቀራቸው ታራሚዎች በግድያ ወንጀል ያልተከከሰሱ፤  የሚያጠቡ እና ነፍሰ-ጡር እናት ታራሚዎች ሲሆኑ ከግድያ በመለስ የተለያዩ ወንጀሎች ውስጥ የተሳተፉ የውጭ ሀገር ዜጎች እንዲለቀቁ እና ወደ የመጡበት ሀገሮች እንዲላኩ መወሰኑን ጠቅላይ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።

በይቅርታው የተካተቱት ታራሚዎች በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ስር ባሉ አምስት ማረሚያ ቤቶች ማለትም በቃሊቲ ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት፣ ቂሊንጦ፣ ሸዋ ሮቢት፣ ዝዋይ እና ድሬድዋ የሚገኙ ታራሚዎች ናቸው ይህ በእንዲህ እንዳለ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለ14 ቀናት ለይቶ ማቆያ እንዲቆዩ የተደረጉ ከውጭ የገቡ መንገደኞች ምግብና ሕክምና እያገኘን ባለመሆኑ ወደ ቤታችን እንሄዳለን በሚል ከፖሊስ ጋር መጋጨታቸውን ኢትዮ ኤፍ ኤም ዘግቧል።

ኢትዮጵያ ከውጭ አገራት የሚገቡ ሁሉም መንገደኞች ወጪያቸውን ችለው በለይቶ ማቆያ እንዲቆዩ ስትወስን የመክፈል አቅም ያላቸው በራሳቸው ወጪ በስካይ ላይት ሆቴል፣በግዮን ሆቴልና በሌሎች ሆቴሎችን እንዲቆዩ በመደረግ ላይ ይገኛል ወጪያቸውን መሸፈን የማይችሉት ግን በአዲስ አበባ ባሉ የመንግስት በትምህርት ቤቶች እንዲቆዩ በመደረግ ላይ ነው።

ይሁንና በቦሌ መሰናዶ ትምህርት ቤት እንዲቆዩ የተደረጉት ከውጭ የገቡ መንገደኞች ግን እስካሁን ምግብ እየቀረበልን አይደለም የህክምና ምርመራም እየተደረገልን አይደለም በማለት መንገደኞቹ ወደቤታችን እንሄዳለን በሚል ከአዲስ አበባ ፖሊሶች ጋር ግብግብ ውስጥ መግባታቸውን ለማወቅ ተችሏል የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ኢንስቲትዩት በበኩሉ መንገደኞቹ ገና መግባታቸው እንደሆነና የምግብ ድጋፉ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመቀናጀት እንደሚቀርብላቸው አስረድቷል፡፡