አባይ ሚዲያ መጋቢት 17፤2012

ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ አዲስ አበባ ውስጥ ተዘዋውረው በሽታውን ከመከላከል ረገድ ያዩት ነገር እንዳሳሰባቸው ገለጹ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ አዲስ አበባ ውስጥ ተዘዋውረው በሽታውን ለመከላከል በሕዝቡ መደረግ ያለባቸው ነገሮች ሙሉ ለሙሉ እየተደረጉ እንዳልሆነ በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ ገልጸዋል።

“የሚጠጋን ቫይረስ የለም ሲሉ የነበሩ አገራት ያሉበትን እያየን አንዘናጋ” ያሉት ፕሬዝዳንቷ የተመለከቱት ነገር ሳያሳስባቸው አልቀረም፤ ስለዚህም በባለሙያዎች የተሰጡ “መመሪያዎችን በመተግበር በኩል ገና ብዙ ይቀረናል” በማለት ጽፈዋል።

ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ጨምረውም የበሽታው ምርመራ በስፋት ባለመደረጉ ያለው ትክክለኛ ሁኔታ ስለማይታወቅ በአገር ደረጃ ተቀናጅቶ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ፕሬዝዳንቷ የማረምያ ቤቶችን መጨናነቅ ለመቀነስ በኮሮና ቫይረስ ሊመጣ የሚችለውን ከፍተኛ ችግር አስቀድሞ ለመከላከል በሕገ መንግሥት አንቀጽ 71/7 መሠረት በቀላል ወንጀል እስከ 3ዓመት ለተፈረደባቸው 4011 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ ማድረጋቸውን በፌስቡክ ገፃቸው ላይ የሰፈረው መረጃ ያመለክታል፡፡

መንግሥት የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ተጨማሪ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑንም ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ገልጸዋል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የተለያዩ መልዕክቶች ቢተላለፉም ልብ የሚላቸው እምብዛም መሆኑ እየተገለጸ ሲሆን ቫይረሱን ለመከላከል በሚልም ዜጎች የሚያደርጓቸው ነገሮች ይበልጥ ተጋላጭ እንዲሆኑ እያደረጋቸው ነው ተብሏል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሸቀጦች ላይ ጭማሪ በሚያደርጉ ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እንደሚወሰድ ከንቲባው ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰድን እርምጃ በቅርብ እንደሚከታተሉት ገልጸዋል።

ምክትል ከንቲባው በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ እንዳሰፈሩት “ጤፍ፣ ሳሙና፣ ውሃና የመሳሰሉት ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የምታደርጉ ነጋዴዎች ድርጊታችሁ ተቀባይነት የሌለው ብቻ ሳይሆን ከሰብአዊነት ውጪ ነው” ብለዋል።

አስተዳደራቸው ይህንን ጉዳይ እየተመለከታተለው መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ከንቲባው “እኔ እራሴ የድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ ከፍ ያለ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ በቅርብ እከታተላለሁ” ብለዋል።

ጨምረውም “እንደ ሰው በሌሎች ችግር ላይ ማትረፍን አንፈቅድም” በማለት ድርጊቶቹ ተገቢ ያልሆነና ለችግር ተጋላጭ የሆኑትን ወገኖችንን የሚጎዳ መሆኑን ገልጸው “ይህንን ፈተና እናልፈዋለን፤ ግለሰቦችና የንግድ ተቋማትም በአስቸጋሪ ጊዜ ለሰብአዊነትና ለፍቅር በሚያደርጉት ተግባራት ይመዘናሉ” ብለዋል።