አባይ ሚዲያ መጋቢት 17፤2012

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድርድር ዙሪያ አሜሪካ ያሳየችው አቋም ከተሰጣት ኃላፊነት በላይ መሆኑን አምባሳደር መለስ ዓለም ተናገሩ በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን፣ የድርድሩን ሁኔታ እና የአሜሪካን የአደራዳሪነት ሚና በተመለከተ ከምሥራቅ አፍሪካ ዘጋቢ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

የምሥራቅ አፍሪካው ጋዜጠኛ ግድቡ ምን ያክል አስፈላጊ እንደሆነ ላነሳላቸው ጥያቄም ኢትዮጵያ ድህነትን ለማሸነፍ ያላት ተስፋ አሁን የምትገነባው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግደብ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

“ኢትዮጵያ ግድቡን ድንገት የገባችበት ሥራ እንዳልሆነ ዓለም ሊገነዘበው ይገባል፤ እ.አ.አ ከ1960 ጀምሮ ጥናቶች ተደርገዋል፤ የሌሎች ሀገራት ዜጎችን ጨምሮ ባደረጉት ጥናት ግድቡ ለታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ጉዳት እንደማያደርስ ነው ያረጋገጡት ብለዋል፡፡

በአሜሪካ ለቀረበው የመጨረሻ ድርድር ኢትዮጵያ ለምን እንዳልተገኘች ሲጠየቁም “አሜሪካውያን የድርድሩ አመቻቾች ናቸው፤ ይሁን እንጅ የአሜሪካ የግምጃ ቤት ዋና ጸሐፊ ራሳቸውን እንደ ዋና ተዋናይ አድርገው መጡ፤ ይህ ትክክል እንዳልሆነ ተገልጧል” ብለዋል፡፡

“ድርድሩ የኢትዮጵያን ጥቅም እስካላስከበረ ድረስም ተገድዳ አትቀበለም፤ ጉዳዩ ሀገርን እና ሕዝብን ዝቅ አድርጎ ማየት ነው፤ የሀገሪቱንም ሉዓላዊነት ተዳፍሯል” ብለዋል ኢትዮጵያ የምትፈልገው ድርድሩ በእውነት ላይ ተመሥርቶ ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ እንዲካሄድ እንደሆነም አስገነዝበዋል፡፡

ግብጽ በየዓመቱ 55 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የውኃ መጠን ማግኘት ትፈልጋለች ያሉት አምባሳደሩ ይህም የዓባይ ወንዝን በብቸኝነት የመጠቀም ፍላጎት በመሆኑ እንደ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ዩጋንዳን እና ሌሎችም የተፋሰሱ ሀገራት እንደማይቀበሉትም አስታውቀዋል፡፡ መተባበር ብቸኛው መውጫ መንገድ በመሆኑ ተባብሮ መሥራት ላይ ሀገራት ቢያተኩሩ እንደሚሻልም ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሊት ጋር በተያያዘ ከግብፅ ጋር  የተፈጠረውን አለመግባባት በሚመለከት በሀገሪቷ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች መግለጫ ሲሰጡ መቆየታቸው አይዘነጋም፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በቅርቡ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ተራማጅ ፓርቲ ለአባይ ሚዲያ በላከው መግለጫ ኢትዮጵያ በውሃ ሀብቷ የመጠቀም፣ የመልማት መብቷንና ሉዓላዊነቷን የሚጋፋ ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖ በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም ብሏል፡፡

በመሆኑም ከዓባይ ውሃ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የተነሳው ጥያቄ ለኢትዮጵያ የሉዓላዊነትና የህልውና ጉዳይ ነው ያለው መግለጫው የዶ/ር ዓብይ መንግስት አሁን የያዘውን አቋም አጠናክሮና ሁሉንም ወገን አስተባብሮ ሉዓላዊነታችንን ማስከበርና ብሔራዊ ጥቅማችንን ማረጋገጥ ይኖርበታል ሲል ፓርቲው አክሏል፡፡