አባይ ሚዲያ መጋቢት 19፤2012

በሆቴሎች ራሳቸውን አግልለው በተቀመጡ ሰዎች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር የላላ ነው ተባለ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ለ14 ቀናት ራሳቸውን በማግለል በሆቴሎች ውስጥ እንዲቀመጡ በተደረጉ እንግዶች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር የላላ መሆኑ ተገለፀ፡፡

መንግስት ባወጣው አስገዳጅ ሁኔታ ምክንያት በአዲስ አበባ የተለያዩ ሰባት ሆቴሎች ውስጥ ራሳቸውን አግልለው የሚገኙ ግለሰቦች እንደተናገሩት በመንግስት በኩል የሚደረገው ክትትል እና ቁጥጥር የላላ በመሆኑ ቫይረሱን ለመቆጣጠር አዳጋች ያደርገዋል፡፡

ለአንድ ወር ያህል በዱባይ ቆታ አድርገው ማክሰኞ መጋቢት 15/2012 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን የገለጹት ምንጫችን ገና ከጅማሬው በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ከፍተኛ እንግልት እንደገጠማቸው ገልፀዋል፡፡

አያይዘውም ባረፉበት ኤሊያና ሆቴል ውስጥ ምንም አይነት ጥበቃ እንዳልተደረገ እና ከቀናት በኋላ ሁለት የጤና ባለሙያዎች በመምጣት የሙቀት መጠናቸውን ለክተው እንደሄዱ አስታውቀዋል፡፡

ምናልባት ቫይረሱ ካለብኝ ቤተሰቦቼን እንዳልበክል በሚል ነው እንጂ ቁጥጥር ባለመኖሩ ወጥቼ ለመሄድ የሚያግደኝ ነገር የለም ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

አስተያየት ሰጪዋ ጨምረው እንደገለፁት ከዱባይ ወደ አዲስ አበባ በገቡ ጊዜ የተቀበላቸው ሰው እንዳልነበረና የተደረገው ጥንቃቄ የጎደለው መስተንግዶ በበሽታው የተያዘ ሰው አየር መንገድ ውስጥ ወዳሉት ሰዎች ለማስተላለፍ የሚችልበት አጋጣሚው ሰፊ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

አቅም ስለሌለን ዋጋቸው የሚቀንስ እንግዳ መቀበያ ሥፍራዎች አሉ፤ እናንተ የጤና ባለሙያዎችን መድቡልን ብንልም የሚሰማን አልነበረም ያሉት ምንጫችን መንግስትም ይህን እያደረገ ያለው ገቢ ለመሰብሰብ ነው የሚመስለው እንጂ ቫይረሱን ለመቆጣጠር አይመስልም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በመጨረሻም የተፈቀዱ ሆቴሎች ዝርዝር እንደተሰጣቸው የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ዝቅተኛ ዋጋው የግዮን ሆቴል 60 ዶላር ቢሆንም ቦታው እንደሞላ ስለተነገረን ከ200 ሰዎች መካከል ስምንታችን የመክፈል አቅም ስለነበረን ወደ ሌላ ሆቴል በማቅናት ራሳችንን አግልለናል ብለዋል፡፡

ቅሬታ አቅራቢዋ እንደተናገሩት ሆቴሎቹም ቢሆን የሚያስከፍሉት ዋጋ ከፍተኛ የሚባል ሲሆን እኔ በግሌ ወደ 32 ሺ የሚጠጋ ብር ለ14 ቀን ሆቴል ውስጥ ራሴን ለማግለል ከፍያለው፡፡

ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚሉት ከሆነ በሆቴሎች ውስጥም ቢሆን ተጋላጭነታችን አልቀነሰም ብለዋል፡፡

አያይዘውም የአንዳንድ ሆቴሎች ሰራተኞቻቸው ጭምር ራስን ለይቶ ማቆየት ምን ማለት እንደሆነ አልገባቸውም ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮቪድ-19 ቅድመ ዝግጁነትና ምላሽ አስተባባሪ አቶ ዘውዱ አሰፋ በበኩላቸው ክፍተቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ አምነው ስለሚደረገው ጥንቃቄ አስረድተዋል፡፡