አባይ ሚዲያ መጋቢት 19፤2012

የአፍሪካ ኅብረት ዋና ጸሐፊ ከኮቪድ-19  ነጻ መሆናቸው ተረጋገጠ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ሙሳ ፋኪ ማሃማት በኮቪድ-19  ስጋት ራሳቸውን ለይተው መቀመጣቸው ትናንት ከተነገረ በኋላ ባደረጉት ምርመራ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው ታውቋል።

ዋና ጸሃፊው በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ እንዳሰፈሩት የምርመራ ውጤታቸው ነጻ መሆናቸውን ቢያረጋግጥም በሚታዘዘው መሰረት ለቀጣዮቹ 14 ቀናት እራሳቸውን ለይተው እንደሚቆዩ ገልጸዋል።

በቫይረሱ መያዙ የተረጋገጠው የዋና ጸሐፊው ባልደረባ ኢትዮጵያ ውስጥ በሽታው ከተገኘባቸው 16 ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት ሞሪሼሳዊው የ72 ዓመት ሰው መሆናቸው ተጠቅሷል።

የአፍሪካ ኅብረት ዋና ጸሃፊው በመልዕክታቸው ላይ በጸሎታቸው ላሰቧቸው ሁሉ ምስጋና አቅርበው፤ አፍሪካ ከበሽታው ጋር የምታደርገው ፍልሚያ ገና መጀመሩን በማመልከት ሁሉም በጋራ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።