አባይ ሚዲያ መጋቢት 21፤2012

የግብፆችን ኢ-ፍትሃዊ አመለካከት ለመቀየር እስከ መጨረሻው መታገል እንደሚገባ ተጠቆመ የግብፆችን ኢ-ፍትሃዊ አመለካከት ለመቀየር እስከመጨረሻው በድርድር መታገል እንደሚገባ የውሃው ዘርፍ ምሁራን አመለከቱ በውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አማካሪ ኢንጂነር ተፈራ በየነ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ግብፆች የአባይ ወንዝ የእነርሱ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ይናገራሉ ይህ ትክክል አይደለም፤ እንደውም አሁን ላይ አባይ የህልውና ጉዳይ የሆነው ለኢትዮጵያ ነው ይላሉ።

ውሃው እንደሚያስፈልጋቸው ባይታበልም፤ ኢኮኖሚያቸው አሁን ባለበት ሁኔታ እነርሱ እንደሚያጋንኑት በአባይ ወንዝ ላይ ጥገኛ አይደለም ያሉት አማካሪው አብዛኛውን ውሃ የሚጠቀሙበት ለእርሻ በመሆኑ ፤እርሻው ለግብፅ አጠቃላይ ምርት ያለው ድርሻ በጣም ውስን ነው ብለዋል ከቱሪዝማቸው ጋር እንኳ የሚስተካከል አይደለም የሚሉት ኢንጂነር ተፈራ ሌሎችም ኢኮኖሚያቸውን የሚያሳድጉበት እና የሚደግፉበት አማራጮች አሏቸው ያሉ ሲሆን ከኢትዮጵያ ሃያ እጥፍ የተሻለ ኢኮኖሚ አላቸው በማለት ያስረዳሉ።

‹‹ሲጮሁ እና ለሌላው ሲያሰሙ ግን የውሃ ዋስትናቸው አደጋ ላይ መሆኑን እና ያለአባይ መኖር እንደማይችሉ ይናገራሉ ኢትዮጵያውያን ዝናብ አላቸው›› ይላሉ፤ በማለት የተናገሩት ኢንጂነር ተፈራ፤ ነገር ግን ኢትዮጵያም ከግብፆች ባልተናነሰ መልኩ በውሃው የመጠቀም መብት እንዳላት እና ወንዙም አሁን ከግብፅ ባልተናነሰ መልኩ የሚያስፈልጋት መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ አማካሪው ገለፃ፤ በእርግጥ ድርድሩ በግድቡ ላይ ቢሆንም፤ አስቸጋሪ ያደረገው ግብፆች ከግድቡ ያለፉ ጉዳዮችን በማንሳታቸው ነው ግድቡ ሃይል አመንጭቶ ውሃው እንደሚለቀቅ ያውቃሉ፤ ፍላጎታቸው ወደ ፊትም ከግድቡ ራስጌ ምንም ዓይነት ልማት እንዳይከናወን ነው ያሉት አማካሪው ይህ ደግሞ ፍትሃዊነት አይደለም ብለዋል።

ስለዚህ ይሄንን ኢ- ፍትሃዊ አመለካከታቸውን እስኪቀይሩ ድርድር በማካሄድ እስከመጨረሻው መታገል ይገባል ሲሉም አክለዋል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሃይድሮሎጂ መምህር እና የድርድር ኮሚቴው አባል ዶክተር ይልማ ስለሺ እንደ ኢንጂነር ተፈራ ሁሉ፤ ግብፆች በውሃው የመጠቀም መብትን ለመንጠቅ ስለፈለጉ እንጂ የግድቡ አሞላሉ እንደማይጎዳቸው ያውቁታል ይላሉ።

የግድቡ አሞላል ጉዳይ ብዙ አያሳስባቸውም ያሉት ዶ/ር ይልማ ይልቁኑ ፍላጎታቸው በቋሚነት የውሃ አለቃቀቁ እንዲወሰን እና በቀጣይ ሌላ ልማት እንዳይኖር ታሳቢ ያደረገ መሆኑን በመጠቆም፤ ይህ ተገቢ ያልሆነ የራስ ወዳድነት አመለካከትን ለመቀየር ያለሌላ ሶስተኛ አካል ጣልቃገብነት በፊት ሲካሄድ በነበረበት መልኩ ድርድር ማድረግ የተሻለ አማራጭ መሆኑን ጠቁመዋል።