አባይ ሚዲያ መጋቢት 21፤2012

በአማራ ክልል ሁለት ኢትዮጵያውያን በኮቪድ-19 በሽታ መያዛቸው ተረጋገጠ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ ባደረገው ተጨማሪ ስልሳ ስድስት (66) የላብራቶሪ ምርመራ ሁለት (2) በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች በማረጋገጡ በአጠቃላይ በሀገራችን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ሃያ ሶስት (23) ደርሷል፡፡

በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡት ግለሰቦች በአማራ ክልል ባህር ዳር ነዋሪ የሆኑ የ37 ዓመት ሴትና በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የአዲስ ቅዳም ነዋሪ የሆኑ የ32 ዓመት ወንድ ኢትዮጵያዊያን ናቸው የአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ከመጀመሩ ዕለት አስቀድሞ አንደኛዋ ታማሚ መጋቢት 10 ከዱባይ እንዲሁም ሁለተኛው ታማሚ መጋቢት 12 ከአሜሪካ የገቡ ናቸው፡፡

ሁለቱም ታማሚዎች የበሽታው ምልክት በማሳየታቸው በላብራቶሪ ምርመራ በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከታማሚዎቹ ጋር የቅርብ ንክኪ የነበራቸውን ሰዎች የመለየትና ክትትል ሂደት እየተከናወነ ይገኛል፡፡

ሁለቱም ታማሚዎች በአማራ ክልል የለይቶ ህክምና መስጫ ማዕከል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል ይህ በእንዲህ እንዳለ የአማራ ክልል ባለፉት ሶስት ሳምንታት ከውጭ ሀገራት ወደ ክልሉ የተመለሱ ዜጎች በየአካባቢያቸው ለሚገኝ የመንግስት የጤና ተቋም ሪፖርት እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ሰጠ፡፡

በአማራ ክልል የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ባወጣው መግለጫ ባለፉት ሶስት ሳምንታ ከውጭ ሀገራት ወደ ሀገር ቤት የተመለሱ እና በአማራ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በአስቸኳይ በየአካባቢያቸው ወደሚገኝ የመንግስት የጤና ተቋም ሪፖርት እንዲያርጉ እና ራሳቸውን እና ያገኟቸውን ሠዎች እንዲያቀርቡ አሳስቧል።

ለክልሉ የገጠር ነዋሪዎች በሙሉ ያጋጠመው ችግር አስቸጋሪ መሆኑን በመረዳት ለግብይትም ሆነ ለሌላ ማህበራዊ ጉዳዮች ወደ ከተማ የሚያደርጉትን ጉዞ በማቆም ባሉበት ሆነው ራሳቸውን እንዲጠብቁ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

የክልሉ ነዋሪዎች አሁን ካለው የወረርሽኙ አሣሣቢ ሁኔታ አንፃር እንደ አስፈላጊነቱ ታይቶ በክልሉ ውስጥ የሚደረግ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቆም ትዕዛዝ ሊሠጥ ይችላልም ነው ያለው መግለጫው።

ከዚህ አንፃርም ይህንኑ በማወቅ በቋሚ የመኖሪያ ቦታቸው ላይ በመሆን ከመንግስት የሚሠጠውን ትዕዛዝ በትኩረት እንዲጠባበቁ ኮሚቴው ማሳሰቡን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት አስታውቋል።