አባይ ሚዲያ መጋቢት 26፤2012

የህዳሴ ግድብን እንደጀመርነው ለማጠናቀቅ ዝግጁ ነን ሲሉ ዶ/ር ደብረጺዮን ገለጹ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን እንደጀመርነው ለማጠናቀቅ የትግራይ መንግስትና ህዝብ ዝግጁ ነው ሲሉ የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ገልጸዋል።

መጋቢት 24 ቀን 2012 ዓ.ም ዘጠነኛ አመቱን ላስቆጠረው የህዳሴ ግድብ የክልሉ ህዝብ ከ652 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ታላቁ የህዳሴ ግድብ ወደኋላ ወደማይመለስበት ደረጃ እንዲደርስ እንደተባበረው ሁሉ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንዲበቃም የትግራይ ህዝብና መንግስት ከጎናችሁ መሆናችንን እናረጋግጣለን ብለዋል።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የሚደረጉ ማናቸውንም ጣልቃ ገብነትና የውዥንብር ፈተናዎች በጋራ አሸንፈን ለመሻገር የክልሉ መንግስት ዝግጁ ነው ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል በተያያዘ ዜና የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን /ሜቴክ/ ተነጥቆ ሌሎች ኮንትራክተሮች ከተሰጠ በኋላ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተሰሩት ስራዎች አመርቂ ናቸው ሲሉ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ገለፀዋል፡፡

እንደ ኢንጂነር ክፍሌ ገለጻ፤ ቀደም ሲል ሜቴክ ከስራው ሲወጣ 25 በመቶ ብቻ የነበረው የኤሌክትሮ መካኒካል ስራዎች አሁን ላይ 44 በመቶ ደርሷል በሜቴክ ሲሰራ የነበረው የሃይድሮሊክ ስቲል ስትራክቸር የታችኛው ክፍል ውሃ ማስተንፈሻ የብረት ስራዎች ጥራታቸውን ያልጠበቁ እና ብየዳቸውም በሙያዊ መንገድ የተገጠሙ ባለመሆናቸው እንዲነሱ ተደርጎ እንደገና በጥራት እየተገነቡ ይገኛሉ።

እያንዳንዱ ብይድም በአልትራሳውንድ እና በኤክስሬይ መሳሪያዎች እየተፈተሸ በሳይንሳዊ መንገድ የሚገነባ ስራ ሲሆን ግድቡ ላይ ቀድሞ የነበረው ብረት እንደነበር ቢቀመጥ ምናልባት 10 ዓመት አገልግሎ እንደገና ከባድ ጥገና ውስጥ የሚያስገባና ሀገሪቱም ላይ ከባድ ኪሳራ የሚያደርስ ነበር ሲሉ ኢንጂነር ክፍሌ ተናግረዋል።

ግድቡ 100 ዓመት ሊቆይ የሚችል መዋቅር ነው ያለው የሚሉት ኢንጂነር ክፍሌ፤ በመሆኑም በግድቡ ግንባታ ጥቅም ላይ የሚውሉ ብረቶች ጥራታቸውን የጠበቁ የመሆናቸው ጉዳይ የግድ መሆኑን አስታውቀዋል እንደ ስራ አስኪያጁ ገለፃ፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ እ.ኤ.አ. ከሶስት ዓመታት በፊት በ2017 መጠናቀቅ የነበረበት ቢሆንም እስከአሁን ያልተጠናቀቀው በኤሌክትሮ መካኒካል ስራውን በሚያከናውነው አካል ጥራት እና የመዘግየት ችግር ምክንያት ነው በአሁኑ ወቅት ስራው በጥራትም ሆነ በፍጥነት በማከናወን ላይ ሲሆን አጠቃላይ የግድቡ አፈጻጸምም 72.4 በመቶ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡