ምንም እንኳን በአኗኗር ዘይቤ፣ በባህልና ምጣኔ ሀብት ከሚለያዩ ሀገራት ተመሳሳይ የሆነ የኮሮና ስርጭትን መከላከያ ዘዴ መጠቀም ቢያዳግትም፤ የብዙ ሀገራት የጤና ባለሙያውችና የመንግስት አካላት የተለያዩ ሀገራትን ተሞክሮ ከህዝባቸው ባህልና ልምድ ጋር በማስታረቅ መፍትሄ ሲያፈላልጉ ይሰተዋላል። 

በዚህም የደቡብ ኮሪያ መንግሥት የኮሮና ተህዋሲ ስርጭትን ለመግታት በወሰዳቸው እርምጃዎችና ባስመዘገባቸው ስኬቶች ምክንያት በብዙ ሀገራት መንግስታት እንደምሳሌ ሲጠቀስ ከርሟል። 

እኔም በዚህ ጽሁፌ በደቡብ ኮሪያ በተግባር የዋሉ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መከላከያ መንገዶችንንና ያመጡትን ውጤቶች፤ እንዲሁም እነዚህን መከላከያ መንገዶች ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር አስማምተን መጠቀም እንድንችል መንግስትና በጤናው ዘርፍ ያሉ ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ህብረተሰቡ ሊወጧቸው የሚገቧቸውን ሀላፊነቶችን እጠቁማለው። 

 የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በኢትዬጲያ

ከቻይና ውሀን ግዛት ድንገት ብቅ ብሎ መላውን አለም ስጋት ውስጥ የከተተውን የኮሮና ቫይረስ በተመለከተ እያደር አስደንጋጭ፣ አሳዛኝና አሰቃቂ እንጂ ይህ ነው የሚባል በጎ ነገር ሳይሰማ ቀናትና ሳምንታት መፈራረቃቸውን ቀጥለዋል፡፡ 

እለት እለት መስፋፋቱን የቀጠለው ይህ ቫይረስ እስከ ዛሬ መጋቢት 26 2012 . ድረስ በጥቅሉ 1,134,421 ያህል ሰዎችን ሲያጠቃ ከነዚህ ውስጥ 236 ሺህ 95 የሚሆኑት ከቫይረሱ ያገገሙ ሲሆን 60 ሺህ 428 በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ለሞት መዳረጉ እየተነገረ ነው፡፡ 

በኢትዬጲያም በመጋቢት 4 2012 የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ መገኘቱን የጤና ሚኒስቴር ካስታወቀበት ቀን አንስቶ እስካሁን ድረስ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 38 መድረሱንና ከነሱ ውስጥም አራቱ ማገገማቸው ተገልጿል። 

መንግስትም በተለያየ ጊዜ ለህብረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን ሲሰጥና በተለያየ ጊዜ ትምህርት ቤቶችን፣ የስፖርት ውድድሮችንና ትልልቅ ስበሰባዎችን ሲያግድ ተስተውሏል።

ነገር ግን በተለያየ ቦታ አዳዲስ ተጠቂዎች ከመገኘታቸው ጋር ተያይዞ ብዙዎች በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በርካታ እንደሚሆኑ ሲገምቱ ይሰማሉ። 

ለዚህም እንደምክንያት የሚያነሱት ምርመራው በጥቂት ሰዎች ላይ ብቻ የተደረገ መሆኑንና በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ወደ ህክምና ቦታዎች ከመምጣታቸው በፊት የነበራቸውን እንቅስቃሴና ንክኪ በአግባቡ የሚከታተል ዘመናዊ መሳሪያም ሆነ የተደራጀ አሰራር አለምዘርጋቱን ይናገራሉ። 

በሌላ በኩል ደግሞ ምንም እንኳን ቫይረሱ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱ ከተነገረበት ቀን አንስቶ መንግስት በተለያየ ሚዲያዎች እንዲሁም የስልክ ጥሪዎችን በመጠቀም ስለ ቫይረሱ ተፈጥሮ እና የአለም ጤና ድርጅት የሚመክራቸውን የመከላከያ ዘዴዎች ቢያስተምርም ማህበረሰቡ እያደረገ ያለው ጥንቃቄ በቂ አለመሆኑን የሚናገሩ ባለሙያችም አሉ።  

የአለም ጤና ድርጅትም ይህ በማይታመን ሁኔታ በአለም ሀገራት እየተሰራጨ ያለው ቫይረስ እንደ ኢትዬጲያ ባሉ ያላደጉ ሀገራት መዛመት ከጀመረ ያለጥርጥር ብዙ እልቂት ሊያስክትል እንደሚችል በመግለጽ ቫየረሱ ቢከሰት ከባድ አደጋ ያደርስባቸዋል ተብለው ለሚታሰቡ ሀገራት የገንዘብና የቁሳቁስ እርዳታ እንደሚያደርግ አስታዉቋል፡፡ 

ኢትዬጲያ ከደቡብ ኮሪያ ምን ትማራለች?  

በጥር መጨረሻ 2012 . የደቡብ ኮሪያ ጤና ጥበቃ ሀላፊ ባስተለላፈው የስብሰባ ጥሪ መሰረት የትላልቅ የህክምና ኩባኒያ ሀላፊዎች፣ የተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤት ሚኒስተሮች እንዲሁም የተላላፊ በሽታ ተመራማሪዎች፤ እያከበሩት የነበረውን አዲስ አመት በመተው በዋና ከተማ ሲኦል ውስጥ በሚገኝ አዳራሽ ውስጥ ተሰብስበዋል። 

በስብሰባውም ላይ አንድ በሀገሪቱ  የተላላፊ በሽታ ቁጥጥር ከፍተኛ ባለሥልጣን አስቸኳይ መልእክት አስተላለፉ፤  በመልክታቸውም በቻይና ውስጥ ተስፋፍቶ የሚገኘው ተላላፊ የኮሮና ቫይረስ ወደ ሀገራቸው እንደገባና በዛ የተሰበሰቡት የህክምና ኩባኒያ ሀላፊዎችና የጤና ተቋማት ተወካዬች ያላቸውን ሀይል ተጠቅመውና ከሁሉ ነገር በላይ ቅድሚያ ሰጥተው በዜጎች ላይ የቫይረሱን ምርመራ ለማድረግና ባላቸው ማንኛውም መንገድ ተጠቅመው ስለ በሽታው ህብረተሰቡን እንዲያሰተምሩ ቃል እንዲገቡላቸው ጠየቁ። 

ንግግራቸውምእናንተ ወደ ውትድርና የምትሄዱ ጦር ሰራዊት ናችሁበማለት ዘጉ። ምንም እንኳን ይህን በሚናገሩበት ወቅት በደቡብ ኮሪያ ውስጥ በይፋ የታወቁ አራት ብቻ ተጠቂዎች ቢኖሩም፤ በቦታው የነበሩት ሀላፊዎችና ተወካዬችም በህዝባቸው ላይ የመጣውን ጠላት ለመዋጋት ያላቸውን እንደሚሰጡ ቃል በመግባት ተለያዩ። 

ይህ በሆነ በአንድ ሳምንት ውስጥ ሁለት የህክምና ኩባኒያዎች መመርመሪያ መሳሪያዎችን እንደሰሩ አስታወቁ። በየካቲት መጨረሻ ላይ የጤና ጥበቃ ሚኒስተር መስሪያ ቤቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለመመርመር በተለያዩ ቦታዎች ላይ ጊዚያዊ ጣቢያዎች እንዳዘጋጀ አስታውቀ። ሰዎች የአለም ጤና ድርጅት ያወጣቸውን የመከላከያ ዘዴዎች በመተገበር ምርመራ በሚደረግባቸው ጣቢያዎች እንዲመረመሩ የሚያዝ አውጅ አወጣ። 

ይህ አውጅ መሰረቱን መከላከል ላይ በማድረግ የአለም ጤና ድርጅት ያወጣቸውን ቫይረሱ እንዳይሰራጭ የሚረዱ ምክሮችን እነዚህም፦ እጅን ለብ ባለ ውሃ እና ሳሙና መታጠብ ወይም ከአልኮል የተሰሩ የእጅ ሳኒታይዘሮች መጠቀም፤ አስፋላጊ ካልሆነ በቀር ህዝብ በተጨናነቀባቸው ቦታዎች አለመሄድ አንድ ሰው በሽታው ቢኖርበትም ባይኖርበትም አፍና አፍንጫን የሚከልል ማስክ ማድርግ እንዲሁም አፍን፣ አፍንጫንና አይንን በፍጽም በእጅ አለመንካትና ሌሎችንም በአዋጅ መልክ በሚዲያና በተለያዩ የቴክኖሌጂ ውጤቶች በመጠቀም አስተላልፏል። 

በማስቀጠልም የጤና ጥበቃ ሚኒስተር ከጠራው ስብሰባ ሰባት ሳምንት በኋላ 290,000 በላይ ሰዎችን በመመርመር 8000 በላይ የሚሆኑ በበሽታው የተጠቁ  ሰውችን በመለየት ከተለያዩ ሀገራት በተሻለ የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ ችለዋል፡፡ ይህም ቁጥር በአለም አቀፍ ሜትር ድህረ ገጽ አሃዝ መሰረት ከአንድ ሚሊዮን ነዋሪዎች 5200 በላይ የሚሆኑት ሰዎች መመርመራዎችን ያሳያል ፡፡ 

ይህ የጅምላ ምርመራ በየካቲት መጨረሻ በቀን ውስጥ በቫይረሱ 900 በላይ ሰዎች ሲያዙ የነበረበትን አሃዝ ዛሬ ወደ 94 ዝቅ እንዲል አድርጎታል። ይህ አሀዝ ማናቸውንም እንቅስቃሴ በማገድና ሰዎች ከቤት እንዳይውጡ በማድረግ የተህዋሱን ስርጭት መቀነሷን ከሚነገርላት ቻይና በተለየ መልኩ አስፈላጊ የሆኑ የእለት እለት እንቅስቃሴዎች ሳይታገዱ ህብረተሰቡ እርቀቱን ጠብቆ በመንቀሳቀስና በበሽታው የተያዙ ሰዎችን በምርመራ በመለየትና በለይቶ ማቆያ በማስቀምጥ ስለመጣ ስኬታማነቱ በተለያዩ አካላት  ሲነገርለት ይሰተዋላል።  

ለምሳሌ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም በዓለም ዙሪያ ያሉ ሌሎች አገራት ከኮሮና  ቫይረስ ጋር በሚያደርጉት ውጊያ ደቡብ ኮሪያና ሌሎች ተመሳሳይ ሀገራት የተጠቅሟቸውን ይህን በጅምላ ምርመራ የማድረግን ተግባር እንዲተገብሩ መክረዋል፡፡

በተያያዘም የደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካንግ ኪንግ ለቢቢሲ በሰጡት መግለጫ ላይበአሁኑ ሰአት ይህን ቫይረስ ለመዋጋት ዋነኛና አማራጭ የሌለው መፍትሔ ሰዎችን በጅምላ የመመርመር አቅም ማሳደግ ብቻ ነውብለዋል።  ምክንያቱም ምርመራው ተህዋሱ ያለበትን ሰው ለመለየትና በተህዋሱ ያለተጠቁ ሰዎች ላይ እንዳያስተላልፍ በለይቶ ማቆያ በማስቀመጥ የጤና ባለመሙያዎች ከተህዋሱ እንዲያገግም ለመርዳት ያስችላቸዋል፡፡

የመፍትሄ ሃሳቦች

ከላይ የደቡብ ኮሪያ ተሞክሮ እንደሚያሳየው ከሆነ የጅምላ ምርመራ ወረርሽኙን ለመቀነስና፤ ሆስፒታሎች ታማሚዎችን ተቀብሎ የማስተናገድ አቅማቸውን ከማጣታቸው በፊት ሊወሰድ የሚገባ ቁልፍ እርምጃ እንደሆነ ነው። 

ይህን ተሞክሮ ወደ ኢትዬጲያ ለማምጣት ዋነኛ ጋሬጣ ሊሆኑ የሚቸሉት አንድም የመመርመርመሪያው መሳሪያ አቅርቦት እጥረትና ኋላ ቀር የሆነ የጤና አጠባበቅ ፖሊሲ መኖሩ በሌላ በኩል ደግሞ የህብረተሰቡ አኗኗርና ባህላዊ ልምዶች  እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ በዛሬ እለት በሰጡት መግለጫቸው እንደጠቀሱት የእንቅቃሴ እገዳው ብዙ ማህበራዊ ቀውሶች መፍጠሩ ናቸው። 

የዓለም ባንክ በፈረንጆች አቆጣጠር 2015 . ባወጣው መረጃ  በኢትዮጵያ ለሚኖሩት 1000 ሰዎች 0.3 የሆስፒታል አልጋዎች ያሉ ሲሆን በጣሊያን ውስጥ ካለው 3.4 በፈረንሣይ 6.5 እና በጀርመን 8.3 ጋር ሲነጻጸር የኮሮና ቫይረስ በፍጥነት ከተሰራጨ ሀገሪቷ የሚገጥማት አደጋ ከባድ እንደሚሆን ያሳያል። 

በኢትዬጲያ ቫይረሱ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን ጤና ጠብቃ ሚኒስቴር በይፋ ከገለጸ ሶስት ሳምንት ቢሆነውም እስካሁን በአማካይ ከአንድ ሚሊዮን ነዋሪዎች ውስጥ 20 የሚሆኑት ብቻ ምርመራ ተደርጎላቸዋል። ይህ ቁጥር ከደቡብ ኮሪያ ከአንድ ሚልዬን በአማካኝ 5200 ምርመራ የተደረገላችው ጋር ሲተያይ ምርመራው ገና በአግባቡ እንዳልተጀምረ የሚያሳይ ነው።   

ይህ በኢትዮጲያ ውስጥ እጅግ የዘገየው እና በደንብ ያልተደራጀው የምርመራ ዘዴ ለዶክተሮች እና ነርሶችም ጭምር አስጊ እንደሚሆን ብዙ የህክምና ባለሙያዎች ተንብየዋል፡፡ 

ምንም እንኳን ከላይ የጠቀስኳቸው ምክንያቶች የጅምላ ምርመራ ለማድረግ እንቅፈቶች ቢሆኑም ማንነንቱ ያልታወቀን ጠላት መዋጋት ትርፉ ድካም ስለሆነ ሁሉም ባለድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ የየራሱን ድርሻ ተወጥቶ ምርመራው የሚካሄድባቸውን መሳሪያዎች በብዛትና በአፋጣኝ ለማግኘት መጣር አለበት። 

ለዚህም የባለ ሀብቶችና በውጪ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጲያውያንና የኢትዬጲያዊያን ወዳጆች ሚና ከፍተኛ ነው የሚል ግምት አለኝ። ምክንያቱም ለኢትዬጲያ ከዚህ የበለጠ ዘር ቀለምና ጾታ ሳይለይ በጅምላ ሊያጠፋ የሚመጣ ጠላት ይኖራታል ብዬ አላስብም። 

ስለዚህ ሁሉም ኢትዬጲያዊ  ካደጉት ሀገራት ተቀብለነው በየቤታችን የምንወዳቸውን ሰዎች እያሳጣን ለዘመናት አብሮን እንደኖረው እንደ ኤችአይቪ ኤድስ ችግሩ የጋራ መሆኑ ቀረቶ የየቤቱ ፈተና ከመሆኑ በፊት ሀላፊነቱን መወጣት አለበት። 

በእርግጥ አሁን ባለው የኢትዬጲያ ነባራዊ ሁኔታ ልክ እንደ ደቡብ ኮሪያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ዜጎች ለመመርመር አዳጋች መሆኑ አይቀርም ነገር ግን የአለም ጤና ድርጅት ያወጣቸውን ቫይረሱ እንዳይሰራጭ የሚረዱ ምክሮችን ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ መተግበርና ህብረተሰቡ ከራሱ ባልተናነሰ መልኩ ተጓድኝ በሽታ ያለባቸውን ሰዎችና አረጋዊያንን በማሰብ ጥንቃቄን እንዲያደርግ ማስተማር ጊዜ የሚሰጠው ነገር አይደለም። 

በጤና ጥበቃ በኩልም አሁን ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ ተጓዦች ብቻ ሳይሆን ቢያንስ በሽታው ከተነሳበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ ሀገራት ጉዙ ያደረጉትን ሰዎች ምርመራ የማድረግ እቅድ መያዝ አለብት። እንዲሁም ቫይረሱ የተገኘባቸውን ሰዎች እንቅስቃሴ በተደራጀ መልኩ የኋልዬሽ ክትትል ማድረግ ። 

በመጨረሻም በተለያዩ ሀገራት የገጠመውን በተለይም በጣሊያን ዋነኛ ምክንያት የሆነውን በጤና ባለሙያውችና የተለያዩ እቃ አቅራቢዎች በኩል የሚተላለፈውን የቫየረሱን ስርጭት በተገቢ ሁኔታ ለመከላከል በቂ የመከላከያ ቁሳቁሶችን በማቅረብ ቀስ በቀስ የትህዋሱን ስርጭት መግታት ይኖርበታል።