አባይ ሚዲያ መጋቢት 27፤2012

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኛ የመቀነስ እርምጃ ተቃውሞ ገጥሞታል የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የተወሰደውን እርምጃ ተከትሎ ገቢው መቀነሱን ያስታወቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ የኮንትራት ሠራተኞችን ቀንሷል፤ የአየር መንገድ የሠራተኞች መሠረታዊ ማህበር በበኩሉ እርምጃውን ተቃውሞታል፡፡

የአየር መንገዱ መሠረታዊ የሠራተኞች ማህበር በላከው መግለጫው፤ ‹‹እየተደረገ ያለው ቅነሳ ወቅቱን ያላገናዘበ፣ መሠረታዊ የሠራተኞች መብትን የጣሰ ነው›› ሲል ወቅሷል አየር መንገዱ መንገደኞችን ማጓጓዝ ቢያቆምም ጭነት እያመላለሰ መሆኑን የጠቆመው ማህበሩ፤ ከዚህም አንፃር ሁሉንም ሠራተኞች ይዞ ማቆየት የሚያስችል ገቢ እያገኘ በመሆኑ ቅነሳው ተገቢ አይደለም ሲል ተቃውሞታል፡፡

የጥገና ክፍሉም የውጭ ሀገር አውሮፕላኖችን እየጠገነ ገቢ በማግኘት ላይ ነው ሲል አክሏል አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ገንዘብ የሚከፍላቸውን የውጭ ሀገር ዜጐች ይዞ እየቀጠለ ኢትዮጵያውያንን ማባረሩም ተገቢ አይደለም ያለው ማህበሩ፤ በዚህ የችግር ወቅት ትርፍን ኢላማ አድርጐ መንቀሳቀሱ ለዜጐች ህልውና አለመጨነቁን አመላካች ነው ብሏል፡፡

50 ኢትዮጵያውያን ሠራተኞችን ከማስወጣት 1 የውጭ ሀገር ዜጋ ተቀጣሪን መቀነስ ይቀል ነበር ያለው ማህበሩ፤ አየር መንገዱ ለዜጐች የሰጠው ግምት አስተዛዛቢ ነው ብሏል በአየር መንገዱ ውስጥ በርካታ ሠራተኞች የኢትዮጵያ ሠራተኛና አሠሪ ህግ ከሚፈቅደው ውጪ በኮንትራት ብቻ ለረጅም አመታት እንዲሠሩ ይደረጋል የሚሉት የሰራተኛ ማህበሩ ሊቀመንበር ካፒቴን የሺዋስ፤ ሆስተሶች፣ ቴክኒሻኖች፣ የቲኬት ቢሮ ሠራተኞችን ጨምሮ በርካቶች ያለ አግባብ በኮንትራት ነው አላቂ ላልሆነ ስራ እንዲሠሩ የሚደረጉት ይላሉ፡፡

ይህም ሠራተኛው እንደ ቋሚ ሠራተኛ መብቱን እንዳይጠይቅ ለማድረግ ታቅዶ መሆኑን የሚያስረዱት ካፒቴን የሺዋስ፤ አሁን ሰራተኞችን የቀነሰበት አግባብም ከህግ ውጪ በሆነ አሠራር ነው ይላሉ ካፒቴኑ ከተባረሩት ሠራተኞች መካከል መሆናቸውን ጠቁመው፤ የተባረሩበት ምክንያትም ‹‹ሠራተኞች በቡድን በማደራጀት፣ የአየር መንገዱን ስም አጠልሽተዋል›› በሚል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በቀጣይም መንግስት ጣልቃ ገብቶ ጉዳዩን የማያስተካክል ከሆነ ተከታታይ ሰላማዊ ሠልፎችን እናደርጋለን፤ በተለያዩ አግባቦች መብታችንን ለማስከበር እንታገላለን፤ ድርጅቱ የግለሰብ ሳይሆን የህዝብ ነው፤ ይሄ መታወቅ አለበት›› ብለዋል በአየር መንገዱና በመሠረታዊ የሠራተኛ ማህበሩ መካከል የተፈጠረውን ችግርም የሚመለከታቸው አካላት እንዲያውቁት መደረጉንም ካፒቴን የሺዋስ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ባስከተለው የኢኮኖሚ ቀውስ ብዙ አየር መንገዶች በኪሳራ ውስጥ ስለሆኑ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞቻቸውን ከሥራ እያሰናበቱ መሆናቸውን ጠቅሶ አየር መንገዱ አንድም ቋሚ ሠራተኛ አልቀነስኩም ሲል የሰራተኛ ማህበሩን ተቃውሞ አስተባብሏል በተለያዩ ድረ ገጾች የሚነገረው መረጃና ስለውጭ አገር ሠራተኞች የሚቀርበው መረጃ ሐሰተኛ መሆኑን አየር መንገዱ ገልጿል፡፡