አባይ ሚዲያ መጋቢት 27፤2012

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሞት መመዝገቡን ኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ ኢንስቲትዩቱ እንዳስታወቀው በኮቪድ-19 ህይወታቸውን ያጡት አንዲት የ60 ዓመት ታማሚ ናቸው፡፡

ታማሚዋ መጋቢት 19 ቀን 2012 ዓ.ም የኮቪድ 19 ምልክት ታይቶባቸው በለይቶ ማከሚያ ገብተው የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው የነበረ ሲሆን በመጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም ቫይረሱ እንደተገኘባቸው መረጋገጡን ኢንስቲትዩቱ ገልጿል ይሁንእንጂ ታማሚዋ ከመጋቢት 22 አንስቶ ላለፉት ስድስት ቀናት በፅኑ ህክምና ላይ የነበሩ ሲሆን በዛሬው እለት ህይወታቸው ማለፉ ተመልክቷል፡፡

ህብረተሰቡ በዚህ ሳይደናገጥ ለተለያዩ ጉዳዮች በአንድ ቦታ መሰባሰብን በማስወገድ፣ እጅን አዘውትሮ በመታጠብ፣ በአካል ንክኪ የሚደረግ ሰላምታን በመተውና አካላዊ መራራቅን (ቢያነስ አንድ ሜትር) ተግባራዊ በማድረግ የበሽታውን ስርጭት እንዲከላከልም የጤና ሚኒስቴርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሳስበዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በህልፈተ ህይወታቸው የተሰማቸውን ሀዘን እየገለጹ ለቤተሰቦቻቸውም መፅናናትን ተመኝተዋል ይህ በእንዲህ እንዳለ በዛሬው እለት በኢትዮጵያ ተጨማሪ አምስት ሰዎች በኮቪድ 19 መያዛቸውን የጤና ሚኒስቴር ገልጿል ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ ባለፈው 24 ሰዓታት ውስጥ 59 የላብራቶሪ ምርመራዎች የተደረጉ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ አምስቱ ሰዎች በኮቪድ 19 መያዛቸው ተረጋግጧል ብሏል።

ሶስቱ ታማሚዎች ኢትዮጵያውያ ሲሆኑ፥አንዱ ኤርትራዊ አንደኛው ደግሞ ሊቢያዊ ናቸውም ነው የተባለው በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠው አምስቱ ግለሰቦች በአዲስ አበባ የሚገኙ መሆናቸው ነው የተነገረው ፡፡

አንደኛው ቫይረሱ የተገኘበት የ26 ዓመት ወጣት ከዱባይ የመጣና በለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበረ፣ ሁለተኛው የ60 አመት ግለሰብ ከኮንጎ የመጣ እና በለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበረ፣ ሶስተኛ የ45 አመት ግለሰብ ከካናዳ የመጣና በለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበረ፣ አራተኛዋ የ27 አመት ወጣት ከእንግሊዝ የመጣች እና በለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበረች እንዲሁም አምስተኛው የ30 አመት ወጣት እና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የነበረው መሆኑ ተገልጿል፡፡

የዛሬውን ውጤት ጨምሮም እስካሁን በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 43 መድረሱን ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል በለይቶ ማቆያ ውስጥ ሆነው ህክምናቸውን የሚከታተሉ ሰዎች ቁጥር 36 ሲሆን፥ 1 ሰው ህይወቱ ሲያልፍ አራት ሰዎች ደግሞ አገግመዋል፤ ሁለቱ ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።