አባይ ሚዲያ መጋቢት 28፤2012

የገዳዩ ኮቪድ-19 ተሕዋሲ የቱጃር፤ ኃያል፣ የዓለም አስገባሪ መንግሥታትን እያስገበረ ሚሊዮኖችን ለክፎ ብዙ ሺዎችን እየፈጀ አስፈሪነቱን ቀጥሏል ሐኪሞች፣ ነርሶች፣ሌሎች የጤና ባለሙያዎች ሕሙማንን ለማዳን ሌት ከቀን እየታገሉ ቢሆንም የቫይረሱ ፈጣን ስርጭት ግን አልተገታም።

የአብዛኛዉ ዓለም ሕዝብ ከየቤቱ እንዳይወጣ፤ ከቅርብ ቤተሰቦቹ ዉጪ እንዳይገናኝ በሕግ ሲታገድ የሐብታሞቹ ሐገራት ምጣኔ ሐብት ሳይቀር እየተሽመደመደ ነዉ ተመራማሪዎችና የመድሐኒት አምራች ኩባንዮች መድሐኒትና ክትባት ለማግኘት እየተጣጣሩ መሆናቸዉን በየአጋጣሚዉ እየተናገሩ ቢሆንም እስካሁን ግን ጠብ ያለ ነገር የለም።

የዓለም ጤና ድርጅት በተደጋጋሚ እንዳስታወቀዉ ተሕዋሲዉ ኢትዮጵያን በመሳሰሉ ደካማ የጤና ሥርዓት ባላቸዉ ሐገራት በስፋት ከተሰራጨ የሚፈጀዉ ሕዝብ ቁጥር ለግምት እንዳያዳግት ያሰጋል የህክምና ባለሙያው ዶ/ር ሲሳይ ለማ በቫይረሱ የተፈጠረውን ስጋትና የወረርሺኙን ስርጭት ማቃለያዉ አንድ መንገድ ብቻ ነው፤ እሱም መከላከል ነው ሲሉ ለአባይ ሚዲያ ይናራሉ፡፡

ዶ/ር ሲሳይ ለመከላከል፣ የኢትዮጵያ መንግስት፣ የጤና ተቋማትና ሕዝቡም ባጠቃላይ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነዉ።ግን ብዙዎች እንደሚሉት በቂ አይደለም ብለውናል ይህ በአንዲህ እንዳለ ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በምትገኘው የዱከም ከተማ በኮቪድ-19 የተያዙ ኢትዮጵያዊት ተገኝተዋል።

የ65 አመቷ የዱከም ነዋሪ ከዚህ ቀደም የጉዞ ታሪክ የሌላቸው በመሆኑ ስጋትን ፈጥረዋል የጤና ምኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በገለጹት መሰረት በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 የተያዙ 44ኛ ሰው የሆኑት እኚህ ግለሰብ ተሕዋሲው ካለበት ሰው መገናኘታቸውም አልተረጋገጠም።

ይህም ታማሚዋ ቫይረሱን ከየት አመጡት፤ እስካሁንስ ከስንት ሰው ጋር ተገናኝተው ይሆን የሚል ጥያቄ ስለሚፈጥር አሳሳቢነቱን ከፍ ያደርገዋል የዶክተር ሊያ መግለጫ «ታማሚዋ በሌላ ተጓዳኝ በሽታ ምክንያት ሆስፒታል ገብተው የነበረ ሲሆን በተጨማሪም የኮቪድ-19 ቫይረስ በሽታ በማሳየታቸው በተደረገላቸው የላብራቶሪ ምርመራ በቫይረሱ የተያዙ መሆናቸውን ማረጋገጥ ተችሏል» ይላል።

በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ከተያዙ ሰዎች ሁለቱ በትናንትናው ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ሌሎች ሁለት ሰዎች ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። አራት ደግሞ አገግመዋል። በአሁን ወቅት 36 ሕሙማን በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንደሚገኙ የጤና ሚኒስቴር መረጃ ይጠቁማል።

እስካሁን የጤና ሚኒስቴር ባረጋገጠው መረጃ መሠረት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ተገኝቷል አዳማ፣ ድሬዳዋ፣ ባሕር ዳር እና አዲስ ቅዳም የተባሉ ከተሞች በኮሮና የተያዙ ሰዎች የተኙባቸው ከተሞች ናቸው።