አባይ ሚዲያ መጋቢት 28፤2012

ኢ-ፍትሃዊ ሃሳቧ የበላይ እንዲሆን በአባይ ወንዝ ላይ የተያዘውን ድርድር ከጫፍ እንዳይደርስ የምትታትረው የግብፅን እንቅስቃሴ፤ በተመለከተና ኢትዮጵያስ ከዚህ በኋላ ምን ማድረግ አለባት የሚለው ላይ የህግ  ባለሙያዎች ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡

በፍትህና የህግ ስርዓት ምርምር ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት አቶ ታደለ ካሳ የአባይ ወንዝን የሚመለከት የተፋሰሱን ሀገራት የሚገዛ የጋራ ህግ አለመኖሩ አለመግባባቶች እንዲቀጥሉና ስምምነት ላይ እንዳይደረስ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በመሆኑም በኢትዮጵያ አነሳሽነት የተጀመረውን የናይል ተፋሰስ የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ በስድስት የተፋሰሱ ሀገራት ተፈርሞ ገዢ ህግ እንዲሆን ኢትዮጵያ ጠንክራ መስራት ይጠበቅበታል ይላሉ፡፡

የናይል ተፋሰስ የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ ማለት ወንዙን በጋራ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚደረግ ሂደት እንደሆነ ያብራሩት አቶ ታደለ ካሳ ስምምነቱንም ስድስት ሀገራት ማጽደቅ ቢኖርባቸውም አሁን ላይ ሶስቱ ሀገራት ናቸው ያፀደቁት ብለዋል፡፡

በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ በቀዳሚነት ያፀደቀች ሃገር ስትሆን ሩዋንዳና ታንዛኒያ ደግሞ ኢትዮጵያን ተከትለው አፅድቀውታል ኢትዮጵያ አሁንም ሶስቱ ቀሪዎቹ ሀገራት ማለትም ኬንያ፣ዩጋንዳና ቡሩንዲ ማዕቀፉን እንዲያፀድቁት ማድረግ ከቻለች ገዢ ህግ ስለሚሆን በአለም አቀፍ ህግ ፊት ለፊትም ተቀባይነት ይኖረዋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር በመቆም ነው መከራከር ያለባት የሚሉት ተመራማሪው ይህም ጥንካሬ ይሰጣል ይላሉ ከአስሩ የተፋሰሱ ሀገራት የህግ ማዕቀፉን አንቀበልም ያሉት ሱዳንና ግብፅ በስምምነቱ ሀገራቱ አሁን እየተጠቀምን ያለነው የውሃ መጠን ጠብታ እንኳን እንዳይነካብን የሚል ዓይነት አንቀፅ ይካተትበት በሚል ምክንያት መሆኑን ያስታወሱት ተመራማሪው እንዲህ ያለው ምክንያት ግን በአለም አቀፍ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ህግ ተቀባይነት ያለው አይደለም ብለዋል፡፡

ጥናት ያደረጉት ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ ለመጠቀም የግብጽን በጎ ችሮታ ወይም ፍቃድ አያስፈልጋትም ከግብፅብም አንፃር በአለም አቀፍ የህግ መርህ ግብፅ አባይን ቀድሜ መጠቀም ጀምሪያለው ብላ የሙጥኝ የምትልበት የህግ መሰረት የለውም ይላሉ፡፡

ከወራት በፊት ግብፅን ኢትዮጵያንና ሱዳንን አደራድራለው ያለችው አሜሪካ በመጨረሻ ከአደራዳሪነት ወጥታ ለግብፅ የሚያደላ መግለጫ እስከመስጠት ደረጃ መድረሷ ይታወሳል በዚህ ላይ ጥናት ያደረጉት ባለሙያዎችም አሜሪካ ከማደራደር አልፋ ወገንተኛ መሆኗ በየትኛውም አለም አቀፍ ህግ ተቀባይነት እንደሌለው ገልፀው አሜሪካ በማደራደር ስም ግብፅን ልትደግፍ የቻለችው ብሄራዊ ጥቅም ስላላት ነው ብለዋል፡፡

በሌላም በኩል በግብፅ ጥያቄ ከወራት በፊት ስብሰባ የተቀመጠው የአረብ ሊግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስብስብም ከሱዳን በስተቀር ጅቡቲን ጨምሮ ሌሎች የሊጉ ሀገራት ግድቡን በተመለከተ ለግብፅ ያላቸውን ወገንተኝነት ያረጋገጡበት እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

ይህም ፖለቲካዊ ወገንተኝነት እንጂ በአለም አቀፍ የህግ ማዕቀፎች የሚደገፍ እንዳልሆነ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉትና የህግ ባለሙያዎች እንደሚሉት በአሜሪካና በአረብ ሊግ በኩል የሚታዩ ወገንተኝነቶች በአለም አቀፍ ህጎች የማይደገፉና ኢትዮጵያንም አንገት ሊያስደፉ የሚችሉ አይደሉም ብለዋል ይሁንና በዲፕሎማሲው በኩል ኢትዮጵያ ትበልጣለች የሚሉት ባለሙያዎቹ ግብፅ ለምትወስዳቸው እርምጃዎች ተመጣጣኝ የሆነ ምላሽና ስራ ከኢትዮጵያ ይጠበቃል ይላሉ፡፡