አባይ ሚዲያ መጋቢት 28፤2012

በቻይና በኮቪድ 19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እንደገና ጨመረ። በትላንትናው እለት ብቻ 39 አዳዲስ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የአገሪቱ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል ይኸ ቁጥር ከቅዳሜ ጋር ሲነፃጸር በ30 ከፍ ያለ ነው የቻይና ብሔራዊ የጤና ኮሚሽን በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ ምልክት የማያሳዩ 79 ሰዎች መገኘታቸውን ገልጿል።

በጥብቅ ቁጥጥር የኮቪድ 19ኝን ሥርጭት ለመግታት የሞከረችው ቻይና ባለሥልጣናት ከውጭ አገራት በሚገቡ ሕመምተኞች እና ምልክት በማያሳዩ ግን ደግሞ ቫይረሱ ባለባቸው ሰዎች ወረርሽኙ እንደገና እንዳይባባስ አስግቷቸዋል።

ምልክት የማያሳዩ ሰዎች በዋናነት የተገኙት ወረርሽኙ በተቀሰቀሰባት የሑባይ ግዛት ነው። በመላው ዓለም በኮቪድ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 1 ሚሊዮን 276 ሺሕ በላይ ሆኗል በዚሁ ወረርሽኝ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥርም 70 ሺህ 328 የደረሰ ሲሆን ከ271 ሺህ 730 በላይ ሰዎች ከቫይረሱ ሙሉ ለሙሉ ማገገም ችለዋል።

በኮቪድ 19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በየቀኑ እየጨመረባት የምትገኘው አሜሪካ እስካሁን ከ336 ሺህ 850 በላይ የቫይረሱ ተጠቂዎችን በማስመዝገብ ከዓለም ቀዳሚነቱን እንደያዘች ነው። በሀገሪቱ የ9 ሺህ 620 ሰዎች ሕይወት በዚሁ ቫይረስ ተቀጥፏል።

ስፔን ከ135 በላይ የቫይረሱ ተጠቂዎችን በማስመዝገብ ከዓለም በርካታ ተጠቂዎች የሚገኙባት ሁለተኛዋ ሀገር ስትሆን ከ13 ሺህ በላይ ዜጎቿን በዚሁ ቫይረስ ምክንያት አጥታለች።

በጣልያን እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 129 ሺህ 948 ደርሷል። ከእነዚህ ውስጥ ከ15 ሺህ 880 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን ይህም ሀገሪቱን ከዓለም በርካታ ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት የሞቱባት ቀዳሚዋ ሀገር አድርጓታል።

በጀርመን ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች በዚሁ ቫይረስ ተጠቂ ሆነዋል፤ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ከ1 ሺህ 580 በላይ ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል በፈረንሳይም 92 ሺህ 840 ሰዎች የኮቪድ 19 ተጠቂ ሆነዋል፤ እስካሁንም ከ8 ሺህ 78 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

በአፍሪካ በአጠቃላይ እስካሁን ባለው መረጃ በኮቪድ 19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ9 ሺህ 30 በላይ ሆኗል። እስካሁን 444 ሰዎች በዚሁ ቫይረስ ሕይወታቸውን ሲያጡ ከ900 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከበሽታው አገግመዋል።

በአህጉሪቱ ከፍተኛው የቫይረሱ ተጠቂዎች የተመዘገቡባት ሀገር ደቡብ አፍሪካ ስትሆን እስካሁን በሀገሪቱ ከ1 ሺህ 650 በላይ የቫይረሱ ተጠቂዎች ተመዝግበዋል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 11 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል እስካሁን የ152 ዜጎቿን ሕይወት በቫይረሱ ያጣችው አልጄሪያ ከአፍሪካ በርካታ ሰዎች የሞቱባት ቀዳሚዋ ሀገር ሆናለች።