አባይ ሚዲያ መጋቢት 29፤2012

የኢትዮጵያ መንግስት በበረራ ከሚመጡት መንገደኞች በተጨማሪ በየብስ በኩል ለሚገቡትም ትኩረት አድርጎ ሊመረምርና ሊከታተል እንደሚገባ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ አሳሰቡ።

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኮቪድ-19 ዙሪያ እየተወሰዱ ባሉ እርምጃዎች ዙሪያ ከትናንት በስቲያ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጋር በጽህፈት ቤታቸው መወያየታቸው ይታወቃል።

በውይይቱ ከተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች መካከል የኦፌኮና የመድረክ ሊቀመንበር ዶ/ር መራራ ጉዲና፣ የትዴፓ አመራሩ ዶ/ር አረጋዊ በርኸና የመድረኩ ምክትል ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ይገኙበታል።

ውይይቱ ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ ላይ በሚያሳድረው ተጽዕኖና መንግሥት የሚወስዳቸውን ተጨማሪ እርምጃዎችን አስመልክቶ መደረጉንና ገንቢ ውይይት መኖሩም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስታወቃቸው አይዘነጋም ይህን አስመልክቶ አባይ ሚድያ የውይይቱ ተሳታፊ ለነበሩት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ`ን አነጋግሯል።

ፕሮፌሰር በየነ ወረርሽኙን አስመልክተው የሚወጡ መልዕክቶችን በታቻለ መጠን የተለያዩ ቋንቋዎችን በመጠቀም ማስተላለፍ ይገባል ይላሉ ፓርቲያቸውም ከዚህ አኳያ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ሲሆን፣ ድምፅ ማጉያን በመጠቀምም መልዕክቱን እያደረሰ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ፕሮፌሰሩ በኬንያ በኩል በህገ ወጥ መንገድ ወጥተው የነበሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ አገራቸው በዚያው በኬንያ በኩል እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ እነዚህ ልጆች ወደዱራሜ መዝለቃቸውን ጠቅሰው መላ ቢበጅ መልካም ነው ሲሉ አስገንዝበዋል።

አክለውም መንግስት በዚህ ላይ እንዲሰራ ጠይቀው፣ አገሪቱ ዜጋዋን የትም አትጥልምና ይህን ተከትሎ ለይቶ ማቆያ ቢያንስ በየዞኑ ማዘጋጀት እንደሚገባ ጠቁመዋል የየዞኑን ባለሀብትም በማነሳሳት ይህን ማዘጋጀት እምብዛም እንደማይከብድ መክረዋል።