አባይ ሚዲያ መጋቢት 29፤2012

አርቲስት ግሩም ኤርሚያስ ለታክሲ ባለንብረቶችና ለራይድ ድርጅቶች የእርዳታ ጥሪ አቀረበ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለም ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ እየሆነ መምጣቱ የሚታወቅ ነው;፡ በሀገራችን ኢትዮጵያም መጋቢት 4/ቀን 2012 ዓ ም መከሰቱን ተከትሎ ቫይረሱ የሚያደርሰው ጉዳት ማህበራዊ ቀውስ እንዳያስከትል በሚል ከመንግስት ጀምሮ ሁሉም የህብረተሰብ አካላት የተለያዩ ድጋፎችን ሲያሰባስቡ መቆየታቸው የሚታወቅ ነው፡፡

በተለይ ደግሞ ታዋቂ ሰዎችና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እንዲሁም አርቲስቶች ይህንኑ ድጋፍ የማስተባበር ስራ ሲሰሩ ቆየተዋል በዛሬው ዕለት ደግሞ የኢትዮጵያ ኩላሊት ህመምተኞች ጥምረት በጎ አድራጎት ድርጅት አምባሳደር አርቲስት ግሩም ኤርሚያስ ለታክሲ ባለንብረቶችና ለራይድ አሽከርካሪዎች እንዲሁም ለራይድ ድርጅቶች ዲያሌሲስ ለሚያደርጉ የኩላሊት ህሙማን የነፃ አገልግሎት እንዲሰጡ ጥሪ አስተላልፏል፡፡

አርቲስት ግሩም ኤርሚያስ ከአባይ ሚዲያ የመስመር ላይ የዝግጅት ክፍል ጋር ባደረገው ቆይታ የኩላሊት ህመምተኞች ለኮቪድ 19 በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ በመሆናቸው ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል በሚል ቫይረሱን ለመከላከል የሚረዱ ቁሳቁሶችን እንዳበረከቱላቸው ገልፆ እነዚህ የታክሲ ባለንብረቶችና ማህበራትም ለታማሚዎቹ ድጋፍ እንዲያደርጉ ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡

አርቲስት ግሩም ኤርሚያስ ከዚህ ቀደም በኩላሊት ህመምተኞች ላይ ያተኮረ ፊልም መስራቱ የሚታወስ ሲሆን በዚሁ ዙሪያም የበጎ አድራጎት ስራ ላይ መሰማራቱ ይታወቃል አሁን ደግሞ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ አምባሳደር ሆኖ የበጎ አድራጎት ስራ ከሚሰራበት ድርጅት ጋር በመሆን የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ እንደሚገኝ ገልጧል፡፡