አባይ ሚዲያ መጋቢት 30፤2012

ሰዎችን ከቤት እንዳይወጡ በማስገደድ እንዲተገበር የፖለቲካ አመራሮች  ጥያቄ አቅርበዋል ሰዎች በጣም ካልተቸገሩ በስተቀር ከቤታቸው እንዳይወጡ አስገዳጅ ሁኔታ በመፍጠር  ወረርሽኙን የመከላከሉ ተግባር ሊተኮርበት እንደሚገባ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል የኦፌኮ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ተናግረዋል፡፡

አመራሩ በሽታውን መቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በማተኮር ከመንግሥት ጋር ውይይት እያካሄዱ እንደሚገኙ በመጥቀስ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል ፕሮፌሰር መረራ ቀድሞ መከላከል እንጂ ችግሮች ከሰፉ በኋላ ማወጁ ምንም ጥቅም እንደሌለው ተናግረው፤ ችግሩ ሳይሰፋና በሽታው ሳይሰራጭ ሥራዎች መሰራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

አሜሪካ በመዘናጋት ሀብትና ቴክኖሎጂ ይዛ በርካታ ሰዎች በበሽታው ታምመውባታል ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ኢትዮጵያ ችግሩን ልትሸከመው ስለማትችል ከወዲሁ መሥራት እንደሚያስፈልግና እንደጣሊያንና እስፔን ያሉ አገራት ወረርሽኙ ባደረሰባቸው ተጽእኖ የተነሳ ቀባሪ እስከማጣት የደረሱበት አሳዛኝ ክስተት እንዳይገጥም ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ፕሮፌሰር መረራ ገዥው ፓርቲ ሌሎችን እየከለከለ በየአካባቢው ሰፊ ስብሰባዎች ሲያካሂድ መቆየቱን በማስታወስ እንደ ሐዋሳ፣ ነቀምት፣ ደምቢዶሎ፣ ሆሳዕና በስፋት እስረኞች አንድ ቦታ ላይ ታጉረው መኖራቸውን ትናንት በስልክ መረጃ እንደደረሳቸውም ተናግረዋል ሊቀመንበሩ በየማረሚያ ቤቶች ጥቂት ሰውም ቢሞት የማይረሳ ጠባሳ እንዳይጥልና መንግሥት አስሮ አስጨረሰን የሚል ወቀሳ ከማምጣቱ በፊት መፈታት የሚገባቸውን ሰዎች ሕጉን መሠረት በማድረግ እንዲፈቱ ማድረግ ይገባልም ብለዋል፡፡

ሕዝቡ በመከላከል ሥራው መንግሥትን ለመደገፍ የሚያስችል ሥራ እንዲተገብር፣ ሰው በአንድ ልብ በሽታውን መቋቋም የሚችልበትን ኃይል እንዲያሰባስብ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ በሃይማኖት ተቋማት አካባቢ ያለው ነገር መስተካከል አለበት ያሉ ሲሆን ሰዎች በተቀራረበ መንገድ ወደ እምነት ስፍራ እንዳይጓዙ ሊደረግ እንደሚገባና ሃይማኖትም የሚኖረው ሕይወት ሲቀጥል በመሆኑ የሃይማኖት አባቶች ሁኔታውን ለመቀየር፣ መንግሥትም ሕይወት ለማትረፍ ጠበቅ ያለ ሥራ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአማራ ክልል መንግሥት የቫይረሱ መስፋፋትን ለመግታት እንቅስቃሴዎችን ባገደባት ባህር ዳር ከተማ ለሚገኙ ችግረኞች የምግብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የአባይ ሚዲያ ምንጮች ከስፍራው ገልጸውልናል፡፡

“በዕለታዊ ገቢ የሚኖሩትን ከሰኞ ጀምሮ ቤት ለቤት በመሄድ በነፍስ ወከፍ ስሌት የዱቄት እድላ እየተደረገ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን በተጨማሪም የጎዳና ተዳዳሪዎችንና በቤተ እምነት አካባቢዎች የሚገኙ ችግረኛ ሰዎች በመሰብሰብ መስተዳደሩ በመመገብ ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡