አባይ ሚዲያ መጋቢት 30፤2012

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እየተባባሰ በመምጣቱ ምክንያት መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ያወጣው መግለጫ እንዳለው ይህ ውሳኔ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 መሠረት የተፈጸመ ነው።

መግለጫው እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ጊዜው እንዳስገደደው አመልከቷል ጨምሮም “አገርን ለማዳንና ትውልድን ለመታደግ ከዚህ በላይ ልንወስን እንደምችልም መታወቅ አለበት። ዜጎቻችንም ከዚህ በላይ ግዴታቸውን ለመወጣት ወገባቸውን አጥብቀው መጠበቅ አለባቸው” ሲል አሳስቧል።

መግለጫው ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስለሚቆይበት ጊዜና ስለሚወሰዱ እርምጃዎች ምንም ያለው ነገር የለም ነገር ግን ይህን አዋጅ እንዲያጸድቅ የሚጠበቀው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 4 ቀን 2012 አ.ም ኮቪድ 19 ኢትዮጵያ ውስጥ መግባቱን ተከትሎ ድምጹ ጠፍቶ ከርሟል፡፡

ስብሰባ ማካሄድን መንግስት ቢከለክልም በቪዲዮ ኮንፍረንስ ይሁን በሌላ መንገድ ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ሁኔታ በተመለከተ ጭምር የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፍ ይችል የነበረ ቢሆንም ከሶስት ሳምንት በላይ ዝምታን መርጦ የቆየው ፓርላማው ከአባላቱ ጉትጎታ የተነሳ በቅርቡ ተሰብስቦ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ ሊሰበሰብ ይችላል የሚሉ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ፡፡

በእርግጥ አሁን የተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሀገሪቱ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ እንድታውጅ በህግ ከምትገደድባቸው መካከል አንዱ ነው በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና በኮቪድ 19 ምክንያት ቀጣዩ ምርጫ መራዘም ላይ አስተያየቶች እየተሰጡ ይገኛሉ በህገመንግስቱ መሰረት ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለመጀመሪያ ዙር ማወጅ የሚቻለው ለስድስት ወራት ያህል ሲሆን አሁን ያለው የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ደግሞ ስልጣኑ ከዛ ባነሰ ጊዜ ያበቃል ማለት ነው፡፡

ስለሆነም መስከረም ላይ የሚያበቃው የፓርላማው ስልጣን ካበቃ በኋላ ፓርላማ የመባል ነገር እንደማይኖርና የኮማንድ ፖስት ስልጣን ከፍተኛ በመሆኑ ሀገሪቱ ቢያንስ ለስድስት ወራት በኮማንድ ፖስት ስር ለመተዳደር እንደምትገደድ የህግ ምሁራን ይገልጻሉ፡፡

ሆኖም በሀገሪቱ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲታወጅ ምክንያት የሆነው የኮቪድ 19 መድሀኒት ወይም ክትባት ከተገኘለት ግን አዋጁ ምክንያት ስለሚያጣ እና ፓርላማው በዚያን ግዜ ስለማይኖር የክልል አመራሮችን ሰብስቦ የምርጫውን ግዜ እንደሚያስወስን እና አዲስ በህዝብ የተመረጠ መንግስት እስኪመጣ ግዜ ሀገሪቱን እንደሚያስተዳድር የህግ ምሁራን ይናገራሉ፡፡

ከዚህ ቀደም ከአባይ ሚዲያ ጋር ቆይታ ያደረጉት የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች አቶ ዳውድ ኢብሳ እና አቶ ልደቱ አያሌው እንደገለጹት በህገመንግስቱ መሰረት የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በስልጣን የሚቆይበት ጊዜ አምስት አመት እንደሆነ እየታወቀ የምርጫ ቦርድ የምርጫውን እጣ ፋንታ እንዲወስን በህገመንግስቱ ስልጣን ለሌለው ህዝብ ተወካዮች ም/ቤት መምራቱ አግባብ አይደለም ማለታቸው ይታወሳል፡፡