አባይ ሚዲያ መጋቢት 30፤2012

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ በጎንደር ከተማና አካባቢዋ በፋኖ እና በመንግስት የጸጥታ አካላት መካከል በተፈጠረ ያለመግባባት የሰው ህይወት ማለፉና የአካል ጉዳት መድረሱ ይታወሳል።

በኢትዮጵያ ከተሞች በህዝብ ብዛት ሁለተኛ እንደሆነች የሚነገርላት የጎንደር ከተማ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የጸጥታ ሁኔታዋ ብዙዎች ስጋት ውስጥ መክተቱ ይታወቃል በከተማዋና አካባቢው ያለው ያለመረጋጋትን ተከትሎ የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት አባላት በአካባቢው ወጣ~ገባ እያሉ መሆኑም አይዘነጋም።

የጎንደር ከተማና አካባቢዋ፣ የመንግስት የጸጥታ አካላትና ፋኖን በተመለከተ አባይ ሚዲያ ከወልቃይት~ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ዋናሰብሳቢ ኮለኔል ደመቀ ዘውዱ ጋር ቆይታ አድርጓል አካባቢው ከጦርመሳርያ ግርግር ይልቅ እርስበርስ መስማማትና መሸማገል እንደሚያሻው ኮለኔል ደመቀ ተናግረዋል።

በግጭት የሚመጣ ትርፍ የለም ያሉት ኮለኔሉ በአንድ አገር ሁለት የተለያየ ትጥቅ ሊኖር እንደማይችልም አብራርተዋል ምንም እንኳን ለመንግስት የማይታዘዝና ከመንግስት ጋር የማይስማማ ፋኖ ይኖራል ተብሎ ባይታሰብም፣ አንዳንድ የግል ጥቅማቸውን የሚያራምዱ ፋኖ ነን የሚሉ፣ ነገር ግን የፋኖ ስነምግባር ያልተላበሱ ጥቂት ግለሰቦች እንዳሉ ኮለኔሉ ገልጸዋል።

እነዚህ ጥቂት ግለሰቦችም በሃሳብ በማግባባት ህጋዊነት ተላብሰው እንዲጓዙ ማድረግ እንደሚቻል ኮለኔሉ አብራርተዋል መከላከያ በዚህ ጉዳይ እጁ ባያስገባ የተሻለ እንደሚሆን የገለጹት ኮለኔል ደመቀ፣ የመከላከያ አባላት ሁኔታው በጦርመሳርያ እንፈታዋለን ካሉ ግን ችግሩ ወደ ህዝብ ሊያመራ እንደሚችል ጠቁመዋል።

አክለውም ጎንደር የብዙ የሃይማኖት አባቶችና አዛውንቶች ከተማ መሆኗን ጠቅሰው አስቀደሞ ነገሩ በውይይት ቢፈታ ይህ ካልሆነ ግን መንግስት ለውሳኔው ያመችለታል ብለዋል ኮለኔሉ ፋኖ ማለት ለአገሩ ዳር ድንበር ዘብ የሚቆምና ለህዝቡ መልካም አሳቢ እንደሆነም አብራርተዋል በመጨረሻም ጉዳዩ በተረጋጋ ሁኔታ በውይይት ተፈትቶ ሁሉም ሰው ለአገር ሰላም ሊያስብ እንደሚገባ ኮለኔል ደመቀ አጽንኦት ሰጥተዋል።