አባይ ሚዲያ ሚያዚያ 01፤2012

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በልዩ ሁኔታ ነገ ሚያዚያ 2/2012 ሊሰበሰብ እንደሆነ ታውቋል በልዩ ስብሰባውም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ አባላት ለመሰየም የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብም መርምሮ ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በተለይም አዋጁ ቢያንስ 5 ወራትን እንደሚቆይና በየጊዜው የሚሻሻሉ ድንጋጌዎች እንደሚኖሩት ከጠቅላይ አቃቢህግ የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይዟቸው ከሚመጣው ፖለቲካዊ እንድምታዎች ዋነኛዎቹ የፓርላማው የስልጣን ጊዜ ገደብና የምርጫው እጣ ፈንታ ነው፡፡

የምርጫውን እጣፈንታም ይሁን መስከረም 30/2013 ስልጣናቸው ያበቃል  የተባሉት የምክርቤት አባላት ጉዳይ በምን ማዕቀፍ መፍትሄ ሊያገኝ ይችላል የሚለው ዋነኛ ጥያቄ ሲሆን ህገመንግስቱን ማሻሻል መልስ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የፌደራሊዝም መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ ከአባይ ሚዲያ መስመር ላይ ዝግጅት ጋር ባደረጉት ቆይታ  አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባለበት ሁኔታ ምርጫ ስለማይካሄድ ህገ መንግስቱን ማሻሻ ል መፍትሄ እንደሆነ ነግረውናል፡፡

ዶ/ር ሲሳይ ሌላው ባነሱት ነጥብ መስከረም 30/2013 የገዢው መንግስት ስልጣን ያበቃል የሚለው ስህተት ነው ያሉ ሲሆን አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያውጀው ፓርላማ ማስፈጸም ስለሚኖርበት ስልጣኑም አብሮ ይራዘማል ሲሉ ገልጸዋል፡፡