አባይ ሚዲያ ሚያዝያ 07፤2012

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮና በሥሩ የሚገኙ ሦስት ተቋማት 1,185 ሠራተኞችን ከሥራ ማገዳቸው ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስቷል የቤቶች ልማት ቢሮ፣ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን፣ የቤቶች ዲዛይን ጽሕፈት ቤትና የቤቶች ግንባታ ኢንተርፕራይዝ ከሁለት እስከ 15 ዓመታት ይሠሩ የነበሩ ቁጥራቸው የተጠቀሰውን ሠራተኞች፣ አዲስ የሥራ ምደባ መዋቅር ውስጥ ከሚያዝያ 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ እንዳልተካተቱ ወይም እንዳልተመደቡ የሚገልጽ ዝርዝር፣ በየተቋማቱ ሰሌዳ ላይ ተለጥፎ መመልከታቸውን ሠራተኞች ተናግረዋል፡፡

ኮሜቴዎቹ በወጣው መሥፈርት መሠረት ከሁለት ዓመታት እስከ 15 ዓመታት ሲሠሩ የነበሩ ቋሚ ሠራተኞችን እንደ ችሎታቸውና ብቃታቸው ይመድባሉ ተብሎ ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም፣ ወረርሽኙ ጭንቀት በፈጠረበት ወቅት ከተመደቡት የሚበልጥ ሠራተኞችን ከሥራ ውጪ ማድረግ ምን ማለት እንደሆነም እንዳልገባቸው ሰራተኞቹ አስረድተዋል፡፡

ምድቡ እንዴት እንደተሠራና ለምን ይህ ወቅት እንደተመረጠ እንዳልገባቸው የሚናገሩት ሠራተኞቹ መንግሥት ሠራተኛ እንዳይቀነስ በአዋጅ ከማሳወቁም በላይ፣ እንደ መሥፈርት ተወስዶ ያልተመደቡት ‹‹በነጥብ ተበልጠው›› የሚል ምክንያት መሆኑ እጅግ የሚያስገርምና የሚመለከተው አካል ትኩረት ሰጥቶ ሊያየው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

እነሱም እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የዚህ ወረርሽኝ ሥጋትና ተከታይ ችግሮችን ተጋሪ መሆናቸው ታስቦ፣ የከተማ አስተዳደሩ ወይም መንግሥት መፍትሔ እንዲሰጣቸውና አመዳደቡም እንዲጣራላቸው ጠይቀዋል እስካሁን የተቋማቱ ሠራተኞች ከሥራ ገበታቸው መታገዳቸውን በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ የሰጠው ምላሽ የለም፡፡

በተያያዘ መረጃ በኢትዮጵያ የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማህበር (ወወክማ) የአካል ብቃት አሰልጣኞች በኮቪድ 19  ወረርሽኝ ምክንያት ድንገት ከሥራ በመሰናበታቸው ምክንያት ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት በኢትዮጵያ በቀጣይ ሦስት ወራት ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከሥራ ገበታቸዉ ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ የኢትዮጵያ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር  ዶ/ር ኤፍሬም ተክሌ  ገልጸዋል።

በቫይረሱ ወረርሽኝ መሥፋፋት ምክንያት ሊፈናቀሉ ይችላሉ ከተባሉት መደበኛ ሠራተኞች በተጨማሪ 1.9 ሚሊዮን የሚሆኑት በጊዜያዊነት ኑሯቸዉን የሚመሩ ዕለታዊ ሠራተኞች ሥራ አልባ ሊሆኑ ይችላሉ ያሉት ደግሞ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚንስትር ድኤታ ዶ/ር ተካልኝ ናቸው።