አባይ ሚዲያ ሚያዝያ 07፤2012

በኢትዮጵያ በኮቪድ 19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር ዛሬ በሦስት ጨምሮ 85 መድረሱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ አዲስ በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠው ሦስቱም ሰዎች ወንዶች ሲሆኑ፤ አንደኛው ከአሜሪካ የመጣና በለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበረ ሲሆን ሁለቱ ግን የጉዞ ታሪክ የሌላቸው ቢሆንም በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ የነበራቸው እንደሆኑ ተገልጿል።

ባለፉት ሃያ አራት ሰዓታት ውስጥ በ431 ሰዎች ናሙና ላይ የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ሦስት ሰዎች በኮቪድ 19 መያዛቸው ተረጋግጧል እስካሁን ድረስ በአገሪቱ በአጠቃላይ የኮቪድ 19 ምርመራ የተደረገላቸው 4988 ሲሆን በሽታው የተገኘባቸው ሰማንያ አምስት ሰዎች ናቸው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያ ኮቪድ 19ን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት የሚደግፉ የህክምና ባለሙያዎችን ቻይና ወደ ኢትዮጵያ ልትልክ መሆኑን ሰምተናል ቻይና ከኢትዮጵያ በተጨማሪም የህክምና ባለሙያዎችን ወደ ቡርኪና ፋሶ እንደምትልክ ነው የተገለፀው እነዚህ የህክምና ባለሙያዎች ልምዳቸውን ያጋራሉ እንዲሁም ኮቪድ 19ን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የሚያስችሉ መመሪያዎችን እና ቴክኒካል ምክሮችን ለጤና ባለሙያዎች እና ለህክምና ተቋማት ያካፍላሉ ተብሏል።

በአፍሪካ ሀገራት ያለውን ሁኔታ በትኩረት እየተከታተለች መሆኑን ያስታወቀችው ቻይና ቫይረሱን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የሚያስችሉ መሳሪያዎችን ማቅረቧን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል በሌላ በኩል ቻይና የአሜሪካን ከዓለም ጤና ድርጅት መሸሽ የኮነነች ሲሆን ድጋፏን እንደምታጠናክርም ገልፃለች፡፡

ቻይና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለዓለም ጤና ድርጅት የሚያደርጉትን ድጋፍ በጊዜያዊነት ማቋረጣቸውን ነቅፋ እርሷ ግን ድጋፏን የበለጠ እንደምታጠናክር አስታውቃለች ዶናልድ ትራምፕ ትናንት በሰጡት መግለጫ ‘‘የዓለም ጤና ድርጅት ለቻይና በመወገን ስለኮቪድ 19 በቂ መረጃ አልሰጠንም’’ በሚል አሜሪካ ድጋፏን ማቋረጧን አስታውቀው ነበር፡፡

የቻይና የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ዦ ሊጂያ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ደግሞ ‘‘አሜሪካ ኃላፊነቷን መወጣት ይኖርባታል፤ ቻይናም ጉዳዩን በቅርበት የምታየው ይሆናል’’ ብለዋል‘‘የአሜሪካ ውሳኔ የዓለም ጤና ድርጅትን አቅም የሚያዳክም ነው፤ ዓለማቀፍ ትብብርንም የሚጎዳ ነው ቻይና ግን እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ የዓለም ጤና ድርጅትን በመደገፍም ሆነ ወረርሽኙን በመከላከልና ዓለማቀፍ ትብብርን በማጎልበት በኩል ድጋፏን ታጠናክራለች’’ ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡