አባይ ሚዲያ ሚያዝያ 08፤2012

በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ተጠቂዎች ቁጥር ቀስ በቀስ እየጨመረ 92 መድረሱን የጤና ሚኒስተር ይፋ አድርጓል አንዴ ከፍ አንዴ  ዝቅ እያለ የቀጠለው የሀገሪቱ የመመርመር አቅም እንዳለ ሆነ ቫይረሱ ኢትዮጵያ ውስጥ መግባቱ ከተረጋገጠ ከ35 ቀን በኋላ ነው ወደ መቶ የተጠጋው የተጠቂዎች ቁጥር የተመዘገበው፡፡

በኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ተጨማሪ 7 ሰዎች የኮቪድ 19  እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ለ401 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ ሰባት ሰዎች የኮቪድ 19 እንደተገኘባቸው ጠቅሰው ይህን ተከትሎም በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 92 ደርሷል ብለዋል።

ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰባቱም ግለሰቦች ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፥ ከእነዚህም ውስጥ 6ቱ የጉዞ ታሪክ ያላቸው እና በለይቶ ማቆያ ውስጥ የሚገኙ ሲሆኑ፥ አንዷ ደግሞ የጉዞ ታሪክ የሌላትና ንክኪ እንዳላት በመጣራት ላይ እንደሚገኝ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል በዚህም መሰረት የ21 ዓመት እና የ51 ዓመት እድሜ ያላቻው ኢትዮጵያውን ከአሜሪካ የመጡ፤ እንዲሁም የ76 ዓመት እና የ34 ዓመት እድሜ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ደግሞ ከስዊድን የመጡ ሲሆን፥ ሁሉም በለይቶ ማቆያ ውስጥ የሚገኙ ናቸው።

በተጨማሪም የ32 ዓመት ኢትዮጵያዊ የጀርመንና የቤልጂየም የጉዞ ታሪክ ያለው እንዲሁም የ39 ዓመት ኢትዮጵያዊ ደግሞ ከጃፓን የመጣ ሲሆን፥ ሁለቱም በለይቶ ማቆያ ውስጥ የሚገኙ ናቸው የ14 ዓመት ሴት ኢትዮጵያዊት ደግሞ የጉዞ ታሪክ እንደሌላት የተገለፀ ሲሆን፥ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ እንደነበራት በመጣራት ላይ የሚገኝ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታውቀዋል።

አሁን ላይ 72 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸው በለይቶ ማቆያ ውስጥ ሲሆኑ፥ አንድ ሰው ደግሞ በጽኑ ህክምና ላይ የሚገኝ መሆኑን ሚኒስትሯ አስታውቀዋል ሚኒስትሯ መጭውን የትንሳኤ በዓል ምክንያት በማድረግ የሚካሄዱ የበዓል ግብይቶችም አካላዊ ርቀትን በጠበቀ መልኩ በጥንቃቄ እንዲከወኑም አሳስበዋል።

በተያያዘ መረጃ ገንዘብ የመክፈል አቅም ለሌላቸው 6 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በዩኒቨርሲቲዎች በተዘጋጁ ለይቶ ማቆያዎች ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬተሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን አስታወቁ ዜጎቹ የምግብና የሌሎች ቁሳቁስ አቅርቦት እንደተሟላላቸውም አመልክተው፤በአገሪቱ ቫይረሱን የመመርመር አቅምን ለማሳደግና ለማስፋት በሚደረገው እንቅስቃሴ ደግሞ የምርመራ ማዕከላትን ቁጥር ስምንት ማድርስ እንደተቻለ አቶ ንጉሱ ተናግረዋል።