አባይ ሚዲያ ሚያዝያ 08፤2012

የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የነበሩት አቶ አታላይ ዛፌ ከኮሚቴው መታገዳቸውን የኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ጌጤ አዳል ለአባይ ሚዲያ አረጋግጠዋል፡፡

አቶ አታላይ ዛፌ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴን በመወከል ለአማሪካ ድምጽ በሰጡት ሃሳብ አራት የኮሚቴው አባላት ታስረዋል ማለታቸው አይዘነጋም፡፡

የኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ጌጤ አዳል ለአባይ ሚዲያ እንደተናገሩት የኮሚቴ አባላት በሚል የታሰረ ሰው አለመኖሩንና አቶ አታላይ ከጠቀሷቸው ውስጥ አቶ መብራቱ የተሰኙት የቀድሞ የኮሚቴው አባል የነበሩት ናቸው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ምክትል ሰብሳቢው አክለውም አቶ አታላይ ከኮሚቴው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊነት ከተነሱ የቆዩ መሆናቸውን አብራርተዋል ኮሚቴው ከአቶ አታላይ ጋር ያለውን ችግር ለመፍታት በተደጋጋሚ መልዕክት ቢልክላቸውም ለመነጋገር ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን ነግረውናል፡፡

አባይ ሚዲያ አቶ ጌጤን ኮሚቴው ከተቋቋመበትና አባላቱ ከተሰባሰቡበት አላማ አንጻር ህዝቡ ሌላ ዜና እየጠበቀ በአባላቱ መካከል የመወነጃጀልና የአግድ ደብዳቤ መላላኩ ምን ይጠቅማል የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ሲሆን እሳቸውም በሰጡት ምላሽ ላይ ደብዳቤው የተላከው እንዲማሩበትና ከጥፈታቸው እንዲመለሱ እንጂ አቶ አታላይን በግድ ለመጉዳት የተደረገ አይደለም ብለውናል፡፡

ኮሚቴው ከአማራ ክልል መንግስትም ጋር ያለው ግንኙነት መልካምና ሊበረታታ የሚገባው እንደሆነ ምክትል ሊቀመንበሩ ገልጸዋል አባይ ሚዲያ በዚሁ ጉዳይ ከሃላፊነት ታግደዋል የተባሉትን አቶ አታላይን ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም፡፡