አባይ ሚዲያ ሚያዝያ 10፤2012

በምስራቅ ጉጂ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መታሰራቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ እንደ አካባቢው ነዋሪዎች ገለጻ ከሆነ በምስራቅ ጉጂ 4 ቆላማ ወረዳዎች ማለትም በጎሎ ዶላ ፣ ጉዲ ደረው፣ ሊበን እና ጽባቦሩ ወረዳዎች በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጎሎ ዶላ ነዋሪዎች እንደሚናገሩት አሁን ላይ በአካባቢው ያለው ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸው የመንግስት ሰራተኞች፣ ነጋዴዎች እንዲሁም አርብቶ እና አርሶ አደሮች ጭምር እየታሰሩ መሆኑን ገልጸዋል በተጨማሪም ሰው እርሻ እንዳያርስ ውጡና ሸማቂዎችን አድኑ እንደሚባሉና በዚህ ምክንያት  ትልቅ ችግር ውስጥ መሆናቸውን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

አክለውም እስሩ እየተፈጸመ ያለው በኦሮሚያ ልዩ ሀይል አማካኝነት መሆኑን ይገልጻሉ እስረኞቹም በሀርቀለው ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረው እስረኞቹ ቤተሰብ እንዳይጎበኛቸው መደረጉን እና ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን ገልጸዋል በሌላ በኩል ደግሞ አንድ የነገሌ ከተማ ነዋሪ በነገሌ ከተማም በተመሳሳይ በአካባቢው የሚኖሩ አርሶ አደሮች እንዲሁም በቅርብ ግዜ በኮቪድ 19 ምክንያት ወደቤተሰቦቻቸው የተመለሱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በልዩ ሀይሎች እየታሰሩ ነው ብለዋል፡፡

በተለይም ትላንት እና ከትላንት በስቲያ ከ250 በላይ የሚሆኑ ሰዎች መታሰራቸውን ተናግረዋል ከእነዚህም መካከል 11 የፖሊስ አባላት፣ የዞን እንዲሁም የወረዳ አስተዳደር ካቢኔ አባላትም ለእስር ተዳርገዋል ሲሉም ይናገራሉ የሊበን ወረዳ የጸጥታ ቢሮ ሀላፊ መንግስት እርምጃውን እየወሰደ የሚገኘው በአካባቢው የተለያዩ ወንጀሎች በመፈጸም የሚታወቁ የኦነግ ሸማቂዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በተጨማሪም የህግ የበላይነት ለሁሉም ይሰራል ወንድ ሴት አዛውንት የሚባል ነገር የለም የሀገሪቱ ህግ እንደሚለው ሁሉም ተጠርጠሪዎች ጉዳያቸው የሚመረመር ይሆናል ይላሉ ስለዚህ ሴቶች አልያም አዛውንቶች ለምን ታሰሩ የሚባል ነገር የለም ማንኛውም በወንጀል የተጠረጠረ ሰው በቁጥጥር ስር ውሎ ጉዳዩ የሚመረመር ይሆናል ብለዋል የኦሮሚያ ጸጥታ ቢሮ ሀላፊ ኮሎኔል አበበ ገረሱ መንግስት የእስር እርምጃ እየወሰደ ያለው በታጣቂዎች ላይ እንጂ በሰላማዊ ዜጎች ላይ አይደለም በመሆኑም ከህግ ውጪ የተያዘ ሰው የለም ብለዋል፡፡