አባይ ሚዲያ ሚያዝያ 10፤2012

ባለፈው ሳምንት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጉለሌ ክፍለ ከተማ በከተማው ይኖሩ የነበሩ የአማራ ክልል ተወላጅ የሆኑ የቀን ሰራተኞችንና የጎዳና ልጆችን ወደ ክልላችን ላኩን አሉን የሚል የማያሳምን ምክንያት ያለው ደብዳቤ በማስያዝ ከ5 አዉቶብስ በላይ ሰዎችን ጥንቃቄ በጎደለው መልኩ ወደ ክልላችን እንደበተናቸው መረጃው ደርሶኛል ሲል አስታውቋል፡፡

ቢሮው አክሎም ከ200 በላይ የሚሆኑትም ሚያዚያ 3 ቀን 2012 ዓ.ም ባህር ዳር ደርሰው ወደ ይባብ ካምፓስ እንዲጠለሉ ተደርጓል ብሏል በተጨማሪም ቢሮው ወረርሽኙን ከመከላከል አንጻር እነዚህን ልጆች በተቻለ መጠን በለይቶ ማቆያ እንዲቆዩ ጥረት እንዲደረግ ሲል ለህብረተሰቡ ጥሪ አቅርቦ ነበር ይህንንም ተከትሎ ወደ አማራ ክልል እንዲመለሱ  ከተደረጉ ሰዎች ጋር በተያያዘ ሁለት የስራ አመራሮች ከስራ መታገዳቸው ተገልጧል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጉለሌ ክፍለ ከተማ ይኖሩ የነበሩ እና ከአማራ ክልል የመጡ የቀን ሰራተኞች እና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎችን ከክፍለ ከተማው እና ከሚቀበላቸው አካል ጋር ሳይነጋገሩ ወደ አማራ ክልል በመመለሳቸው በክፍለ ከተማው የወረዳ ስምንት የፀጥታና ሰላም ክፍል የስራ ሃላፊዎች ከስራ መታገዳቸው ታውቋል፡፡

የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ በላይ ደጀን ተገቢውን ቅደም ተከተል ሳይከተሉ እና በደብዳቤው ውስጥ የጎዳና ተዳዳሪዎች ተብሎ የተጠቀሰው ስህተት መሆኑን ገልፀዋል ዋና ስራ አስፈፃሚው አያይዘውም የወረዳው አመራሮች ጉዳዩ እስኪጣራ ድረስ ከሥራ ገበታቸው መታገዳቸውን ጨምረው ገልፀዋል፡፡

በክፍለ ከተማው ውስጥ ባሉ በሌሎች ወረዳዎች ከዚህ በፊት ከክፍለ ከተማው እና ከከተማ አስተዳደሩ ውጪ ሰዎችን ወደመጡበት የመመለስ ተግባር ከመፈፀሙ ጋር ተያይዞ በውል የሚታወቁ እንዳሉ ተጠቁሟል፡፡

በዚህም ምክንያት በውል የታወቁ የተመለሱ ሰዎች ብዛትና የሄዱበት ቦታ እየተለየ ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ደቡብ ክልል ከ190 በላይ ሰበጥዎች በላይ እንዲሁም ቅዳሜ ሚያዚያ 3/2012 ዓ/ም ወደ አማራ ክልል የተላኩ 252 ሰዎች መሆናቸውን ስራ አስፈፃሚው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

በጥቅሉ 442 ተመላሾች መሆናቸው ታውቋል ሚያዚያ 3/2012 ዓ/ም ወደ አማራ ክልል ከተመለሱት ሰዎች ጋር በተያያዘ የአማራ ክልል የሰራተኛና ማህበራዊ ቢሮ  ቅሬታውን ከማሰማቱ ጋር ተያይዞ የጉለሌ ክፍለ ከተማም ትክክል መሆኑን በማመን  በክፍለ ከተማው በወረዳ 8 የሚኖሩ  ከሌላ ክልል የመጡ ሰዎች እንዲመለሱ ያደረጉ የክፍለ ከተማው ሁለት አመራሮች ጉዳዩ እስኪጣራ በሚል ከስራ እንዲታገዱ ተደርጓል፡፡