አባይ ሚዲያ ሚያዝያ 12፤2012

የኮቪድ-19 ወረርሺኝን በመደበኛው ህግ ለመቆጣጠር እቸገራለሁ ያለው የኢትዮጵያ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካጸደቀ ቀናት ተቆጥረዋል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በባህሪው አዋጁ ጸንቶ በስራ ላይ እስከሚቆይበት ጊዜ ድረስ በመደበኛነት ሲሰራባቸው የነበሩ ህጎች ሊጣሱ የሚችሉበት እንደሆነና ከመንግስት አካላት የስራ አስፈጻሚው አካል ሰልጣኑን በበላይነት እንደሚይዝ የህግ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

የህግ ባለሙያው አቶ አዲሱ ጌታነህ ከአባይ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የእስካሁን ማብራሪያዎች ሲታዩ በተለይም ክልከላዎች በግልጽ ሳይቀመጡ ቅጣቶችን መዘርዘር እንደ ዋና ክፍተት ይታያል ብለዋል፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ሀገሪቱን እያስተዳደረ ያለው ኮማንድ ፖስት ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ ቢወስድና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ቢፈጽም ለማን አቤት ይባላል የሚለው ጥያቄ በብዙዎች አዕምሮ ዘንድ እየተመላለሰ ነው፡፡

አቶ አዲሱ እንደሚሉት ከሆነ ኮማንድ ፖስቲ አላማውን ቢስትና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ቢፈጸሙ ሊቆጣጠር የሚችል ቦርድ ይኖራል ነገር ግን እስካሁን በዚህ ደረጃ ግልጽ የተደረገ ማብራሪያም ይሁን የተቆጣጣሪ ቦርዱ አመሰራረት ባይታወቅም የመብት ጥሰቶችን ቅሬታ ግን ሊሰማ እንደሚገባ አቶ አዲሱ አብራርተዋል፡፡