አባይ ሚዲያ ሚያዝያ 13፤2012

በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካዊያን የተሻለ ህክምና ለማግኘት ወደ ሕንድ የሚጓዙ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ደግሞ አገሪቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ከአንድ ነጥብ ሦስት ቢሊየን በላይ ሕዝቧ ከቤት እንዳይወጣ እና ማንኛውም እንቅስቃሴ እንዳይደረግ አግዳለች ይህን ተከትሎም ለህክምና ወደ አገሪቱ የሄዱ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው መመለስ ባለመቻላቸው ከባድ ችግር ላይ እንደሚገኙ  ገልፀዋል።

ዘውዲቱ ንጉሴ የመቅኔ ንቅለ ተከላ ወይም ‘ቦንማሮ ትራንስፕላንት’ የሚባል ህክምና ለማግኘት ነበር ለሁለት ሳምንታት ወደ ሕንዷ ዋና ከተማ ኒው ደልሂ ያቀናችው ዘውዲቱ የደርሶ መልስ የአውሮፕላን ትኬት ብትቆርጥም በሕንድ እንቅስቃሴ እንዳይኖር በመታወጁ ካሰበችው በላይ ለተጨማሪ ቀናት እንድትቆይ ተገዳለች።

“የተወሰነ ገንዘብ ብቻ ነበር ይዤ የመጣሁት፤ ግን የእንቅስቃሴ ገደቡ ከታወጀ በኋላ መንቀሳቀስ ስላልተቻለ ካሰብኩት ጊዜ በላይ በቀን 1000 ሩፒ እየከፈልኩኝ እንድቆይ ተደርጌለሁ ፤ እጄ ላይ ያለው ገንዘብ አልቋል። አላስፈላጊ ወጪ እና እንግልት እየደረሰብኝ ነው” ትላለች”አጋጣሚ ሆኖ ለትምህርት የመጡ የማውቃቸው ሰዎች በመኖራቸው አገር ቤት ስሄድ የምከፍላቸው ገንዘብ ሰጥተውኛል” በማለት ስላለችበት ሁኔታ ታስረዳለች።

ከአንድ ቤተሰብ ለህክምና ሦስት ሆነው የመጡ ሌሎች ኢትዮጵያንም ያሉ ሲሆን እህቱንና እና አባቱን ለማሳከም የመጣው ጌታቸው ሹሜ ስላሉበት ሁኔታ፤ “እህቴ በጣም ብዙ መድሃኒት ነው የምትወስደው፤ ለዚያም ደግሞ በቂ ምግብ መመገብ አለባት። እዚህ ያለው ምግብ ብዙም የሚስማማ አይደለም፤ ብዙ መድሃኒት ወስዶ ምግብ አለመመገብ ከባድ ነው” ሲል ይገልጻል።

ሌላኛው ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ታካሚም “ምግብ ለማግኘት በጣም ተቸግረናል። የታሸገ ምግብ ለመግዛት እየፈራን ነው ወደ ውጭ የምንወጣው። ሁኔታው ከቀን ወደቀን እየከበደን ነው። በየቀኑ የቤት ኪራይ ብቻ ነው እያሰላን ያለነው” ሲል በፈተና ውስጥ እንዳሉ ይናገራል እነዚህ ታካሚዎች የቀደመ የጤና እክል የነበረባቸው መሆኑ ደግሞ ለኮቪድ-19 ወረርሺኝ ያላቸውን ተጋላጭነት ከፍተኛ በመሆኑ ይህም ሌላ ጭንቀት ሆኖባቸዋል።

ዘውዲቱ “ያረፍንበት ሆቴል ያን ያህል ግድ ያለው አይደለም፤ ያለው ነገር በጣም የሚያስፈራ ነው። ህክምና ቢያስፈልገን ከሃኪም ቤት መኪና ካልተላከልን በስተቀር መሄድ አንችልም። የምንፈልገውን በቅርበትና በፈለግነው ሰዓት አናገኝም” ትላለች።

ዘውዲቱ ጨምራም “ቢያንስ የመጀመሪያው የእንቅስቃሴ ገደቡ 21 ቀኑ እንዳለቀ ወደ አገር ቤት በረራ ይጀመራል ብለን ተስፋ አድርገን ነበር ተደጋግፈን ተጋግዘን ነገሮችን እያለፍን የነበረው። በድጋሜ ይራዘማል የሚል በፍጹም አልጠበቅንም ይሄ ነገር ሲሆን ግን ለእኛ ዱብዳ ነው” ስትል ትናገራለች እነዚህ በተለያዩ የሕንድ ግዛቶች በሚገኙ ሆስፒታሎች የሚታከሙ ኢትዮጵያውያን በኒው ዴልሂ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አሳውቀው መልስ እንዳላገኙ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡