አባይ ሚዲያ ሚያዝያ 14፤2012

የህዳሴ ግድቡ የውኃ ሙሌትን አስመልክቶ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በአሜሪካ ዋሽንግተን ከተማ ሲያደርጉት በነበረውና በተቋረጠው ድርድር ስምምነት የተደረሰባቸው ጭብጦች፣ ቀጣዩን ድርድርና የውኃ ሙሌት ለማከናወን ከግንዛቤ እንዲወሰድ ይገባል ስትል ሱዳን አስታውቃለች።

የሱዳን መንግሥት ይኼንን ያስታወቀው ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ከግብፅ መንግሥት የግብርናና የውኃ ሀብት ሚኒስትሮችና ከግብፅ ብሔራዊ ደኅንነት ኃላፊ ጋር፣ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በካርቱም ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ነው።

የሁለቱ አገሮች ኃላፊዎች የተቋረጠውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ በተመለከተና ድርድሩ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ማድረጋቸውን የገለጸው መግለጫው፣ ከዚህ በተጨማሪም በሁለቱ አገሮች የሁለትዮሽ የትብብር ጉዳዮች ላይም መምከራቸውን አመልክቷል።

በውይይታቸው ወቅትም የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ የህዳሴ ግድቡ የውኃ ሙሌትን አስመልክቶ፣ በአሜሪካና የዓለም ባንክ ታዛቢነት በዋሽንግተን ሲደረግ በነበረው ድርድር ስምምነት የተደረሰባቸው ጭብጦች፣ በቀጣይ ለሚደረገው ተመሳሳይ ድርድርና የውኃ ሙሌቱን ለማከናወን ከግንዛቤ እንዲወሰድ መንግሥታቸው ፅኑ ፍላጎት ያለው መሆኑን አስረግጠው መናገራቸውን መግለጫው ያመለክታል።

ከዚህ በተጨማሪም እ.ኤ.አ. በ2015 በሦስቱ አገሮች መሪዎች የተፈረመው ህዳሴ ግድቡን የተመለከተው የመርህ መግለጫ ስምምነት ሱዳን አጥብቃ የምትገዛበት ስለመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ መግለጻቸውን የሱዳን መንግሥት በመግለጫው አስታውቋል።

የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስተር በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያና ግብፅ በመጓዝ የተቋረጠው ድርድር በሚጀምርበት ሁኔታ ላይ፣ ከሁለቱ አገሮች መሪዎች ጋር ለመምከር ፕሮግራም መያዛቸውንም መግለጫው ያመለክታል።

የአሜሪካ የገንዘብ ተቋም ኃላፊ ስቴፈን ምኑቺን ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ጋር የህዳሴ ግድቡ ድርድር በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ በስልክ መወያየታቸውን፣ ከሦስት ሳምንት በፊት መዘገባችን አይዘነጋም።

ሁለቱ ወገኖች ባደረጉት በዚህ የስልክ ውይይትም የህዳሴ ግድቡን ድርድር በፍጥነት ማጠናቀቅ አስፈላጊነት ላይ መግባባታቸውን፣ የኮሮና ቫይረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ እያደረሰ ያለውን ጉዳት መንግሥታት ተቆጣጥረው ቀልባቸውን ከሰበሰቡ በኋላ፣ ድርድሩን ከተቋረጠበት ማስቀጠል ተገቢ ስለመሆኑ ሐሳብ ተለዋውጠው ነበር።

ከዚህም በመቀጠል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በስልክ መወያየታቸውን፣ አሜሪካ ሱዳንን ከአሸባሪነት ዝርዝር ውስጥ ለመሰረዝ በያዘችው ዕቅድ ላይ መምከራቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ያመለክታል።

ሱዳን የህዳሴ ግድቡን አስመልክቶ ለመያዝ የፈለገችውን ሚና አስመልክቶ የተጠየቁት የኢትዮጵያ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ስለሺ በቀለ ፣ ኢትዮጵያ የሱዳንን ፍላጎት በበጎ እንደምትመለከተው ገልጸዋል።