አባይ ሚዲያ ሚያዝያ 14፤2012

የኮቪድ 19 የወረርሽኝ ስርጭትን በአጭር ጊዜ ውስጥ መቆጣጠር ካልተቻለ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ፕሮግራማቸውን ወደሚቀጥለው የትምህርት ዘመን ሊራዘም እንደሚችል የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጠቁሟል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ደቻሳ ጉርሙ እንደተናገሩት፣ እስከ አሁን ባለው ሁኔታ የዩኒቨርስቲዎች የትምህርት ሂደት እንዴት መሆን እንዳለበት እና ወደ መደበኛው የትምህርት አካሄድ ሂደት መመለስ ይቻል አይቻል የሚለው አልተወሰነም።

ምክንያቱም ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ በጤና ሚኒስቴር ይፋ የሆነው መጋቢት2/2012 ሲሆን ከዛ በኋላ ለአስራ አምስት ቀናት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በጊቢያቸው ውስጥ ነበሩ።

ነገር ግን ተማሪዎቹ ወደመጡበት እንዲመለሱ ከተደረጉ አስራ አምስት ቀን እንደመሆኑ ውሳኔ ላይ አልደረስንም ብለዋል።

እንደታሰበው የወረርሽኙ ስርጭት በአጭር ጊዜ መቆጣጠር ካልተቻለ እና ስርጭት መጠኑ በከፍተኛ ሁኔት ከጨመረ በሽታውን ስርጭትን የተማሪዎች ወደ ዩኚቨርስቲው መመለሳቸው ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ማስከተሉ ስለማይቀር የትምህርት ጊዜው ወደሚቀጥለው ዓመት ሊዘዋወር እንደሚችል ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ግን የወረርሽኙ ስርጭት በአጭር ጊዜ የሚገታ ሆኖ ከተገኘ የእረፍት ጊዜን በመጠቀም ማለትም ወደ ክርምት በመግፋት እና ትምህርት አሰጣጡን በማሸጋሸግ ወደሚቀጥለው ዓመት ማለትም 2013 ሳይገባ በወጣለት መርሃ ግብር ለማገባደድ እንደታሰበ ሚኒስቴሩ አሳውቋል።

ሚኒስቴሩ እንደገለፀው፣ ትምህርት አሁን ባለው ወረርሽኝ ምክንያት እንዲቋረጥ እንደተደረገ እና ይህም ደግሞ በትምህርት ሴክተሩ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ እንደ አገር ወረርሺኙን ለመግታት የተወሰደ እርምጃ ነው ተብሏል።

በተለይም የለይቶ ማቆያ በመሆን እያገለገሉ ካሉት ተቋማት መካከል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዋነኛ መሆናቸው መገለፁም ተወስቷል በኢትዮጵያ ያሉ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በዋነት ትኩረታቸውን ወረርሽኙን በመግታት ላይ እንዳደረጉ የጠቀሰው ሚኒስቴሩ፣ በተለይም ደግሞ የእጅ ማጽጃ ሳኒታይዘሮችን እና ከፍተኛ የጤና ድጋፍ የሚያደርጉ የምርምር ሥራዎችንም በማድረግ ላይ እንደሆኑ አስታውቋል።

በተለይም ደግሞ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ በቫይረሱ ለተጠቁ እና በጽኑ ሕሙማን ሕክምና መስጫ ክፍል ለሚገኙ ሰዎች የሚውል የመተንፈሻ ቬንቲሌተር እንደተሠራ አስታውቋል።

ከዚህም ባሻገር የከፍተኛ ትምህርት መምህራንም ወረርሽኙን ለመግታት በበጎ ፈቃድ ተግባር ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ እና ከትምህርት መርሃ ግብሩ ባሻገር ወረርሽኙን መግታት ላይ ትኩረት እንደተሰጠ ጠቁሟል።