አባይ ሚዲያ ሚያዝያ 17፤2012

በርካታ ሰዎች በኮቪድ 19 ከተያዙባት ጎረቤት አገር ጂቡቲ የሚመጡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ፤ የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር የአፋርና አማራ ክልሎች ጥረት እያደረጉ መሆኑን አመለከቱ የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ያሲን ሙስጠፋ እንደተናገሩት፤ “ከጅቡቲ ከበሽታው የሚሸሹ እንዲሁም ጾም ስለሆነ ሙቀቱን ለማሳለፍ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ በርካታ ሰዎች አሉ” ብለዋል።

መንግሥት የቫይረሱን መስፋፋት ለመቆጣጠር በድንበሮች በኩል የሰዎች እንቅስቃሴን ቢያግድም ከጂቡቲ “የሚገቡት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው” ይላሉ ኃላፊው ከጅቡቲ በአፋር ክልል በኩል ወደ ኢትዮጵያ የሚያስገቡ አስራ አምስት የመግቢያ በሮች ሲኖሩ ሦስቱ ዋና የሚባሉ መሆናቸውን ያመለከቱት ኃላፊው በሁሉም ላይ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ከአፋር ክልል ጋር ወደሚዋሰነው የአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ከጅቡቲ በኩል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የዞኑ የጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ካሊድ ሙስጠፋም አረጋግጠዋል ኃላፊው እንዳሉት ሰዎቹ በእግር ድንበር ተሻግረው የሚገቡባቸው የተለያዩ ቦታዎች መኖራቸውን አመልክተው “አንዱ ባቲ ወረዳ ነው።

ባቲ ላይ አቢላል የሚባል ቦታ በተለይ በእግርና በመኪና ሰዎች ስለሚገቡ የሙቀት ልኬት ጀምረናል” ሲሉ የበሽታው ምልክቶችን ለመለየት እየሞከሩ መሆኑን ተናግረዋል በዞኑ ካሉት ሰባት ወረዳዎች አምስቱ ከአፋር ክልል ጋር ስለሚዋሰኑ “ከጅቡቲ በአፋር በኩል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር በርካታ በመሆኑ አራቱ ወረዳዎች ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ የስጋት ቀጠና ናቸው በሚል ተለይተዋል” ሲሉ የዞኑ ጤና ኃላፊ አቶ ካሊድ አመልክተዋል።

እስካሁን አንድ ሰው በቫይረሱ መያዙ የተረጋገጠበት የአፋር ክልል “18 የለይቶ ማቆያ ስፍራዎች ተዘጋጅተዋል” ያሉት የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ያሲን ሃቢብ በተለይም ደግሞ በሦስቱ ዋና ዋና መግቢያዎች በኩል ብዛት ያላቸው ሰዎች በመኪናና በእግር ስለሚገቡ ትኩረት መደረጉን አስረድተዋል።

በአገሪቱ በተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት የድንበር መግቢያዎች ዝግ ቢሆኑም ከጂቡቲ የሚመጡ ኢትዮጵያዊያንን መመለስ ባለመቻሉ እስካሁንም ክልሉ ከጅቡቲ የሚመጡ ሰዎችን ለመቆጣጠር ወደ 380 የሚሆኑ ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲገቡ ማድረጉንና ከለይቶ ማቆያ ለመውጣት የሚሞክሩ በመኖራቸው ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግ ጨምረው ገልፀዋል።

በሌላ በኩል የኢምግሬሽን ዜግነት እና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ የኮቪድ 19 ምርመራ ሳያደርጉ በህገወጥ መንገድ ከጀቡቲ የመጡ እና በጋላፊ ኬላ በኩል ወደ ሀገር ለመግባት የሞከሩ 26 ሰዎችን መያዙን መዘገባችን ይታወሳል፡፡