አባይ ሚዲያ ሚያዝያ 19፤2012

ከወራት በፊት በሶማሌ ክልል አንድ የቻይና ድርጅት የነዳጅ ቁፋሮ በሚያካሂድበት አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ምንነቱ በግልፅ ላልታወቀ የጤና እክል እየተጋለጡና እየሞቱ መሆኑን ዘጋርዲያንን ዋቢ አድርገን መዘገባችን ይታወሳል በቆራሄይ ዞን፣ ሽላቦ፣ ደቦ ወይን እና ጎዴ በተባሉ አዋሳኝ ቦታዎች ችግሩ እንደተስተዋለም ተገልፆ ነበር። በአካባቢዎቹም በቋሚነት የሚኖሩና ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ አርብቶ አደር ማኅበረሰቦች ይገኛሉ።

ዘጋርዲያን በዘገባው ምንነቱ ያልታወቀው ይህ በሽታ በስፋት ተሠራጭቶበታል በተባለው አካባቢ ደቦ ወይን ካሉ ነዋሪዎች አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት “አንድ ሰው ለሳምንት ሊታመም ይችላል፤ ዓይኑ ቢጫ ይሆናል ከተወሰነ ቀን በኋላ ወደ ሆስፒታል ቢሄድም በሽታው ምን እንደሆነ እንደማይታወቅ ይነገረዋል ከዚያም ህይወቱ ያልፋል፡፡

ከጤና እክሉ በተጨማሪም እጅና እግር የሌላቸው የማይናገሩ ልጆች ይወለዱ እንደነበርና ነዋሪዎቹ ችግራቸው ሳይፈታ ዓመታትን መግፋታቸውን ጭምር መናገራቸውን ጋዜጣው ዘግቦ ነበር ከወራት በኋላ ምላሽ የሰጠው የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሶማሌ ክልል ከተፈጥሮ ጋዝ ልማት ጋር በተያያዘ ‘በሰው ላይ ጉዳት ደርሷል’ በሚል የቀረበው ዘገባ መሰረተ ቢስ ነው ብሏል፡፡

ተቋሙ በመግለጫው እንዳስታወሰው፤ ዘጋርዲያን እ.ኤ.አ የካቲት 20 ቀን 2020 እትሙ ‘በኦጋዴን ካሉብና ሂላላ በተባሉ አካባቢዎች እየተካሄደ ባለው የተፈጥሮ ጋዝ ልማት ምክንያት በተከሰተ የውሃ መበከል በአካባቢው ህዝብ ላይ በሽታ በማስከተል እስካሁን ከ2 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል’ የሚል ዘገባ አውጥቷል።

የቀረበውን ዘገባ ለማጣራት ከአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን እንዲሁም ከሌሎች አካላት የተውጣጣ የጥናት ቡድን የተፈጥሮ ጋዝ በሚለማበት አካባቢ ማጣራት ማድረጉን ሚኒስቴሩ አስታውቋል ኤጀንሲው እንዳለው የተፈጥሮ ጋዙን የሚያለማው ፖሊ ጂሲል ኩባንያ ወደ አካባቢው ከገባ በኋላ ሙቀት መጨመር፣ ዝናብ መጥፋትና የተለያዩ የአየር ንብረት ለውጦች መታየታቸውንና አዳዲስ በሽታዎች መከሰታቸውን የአካባቢው ማህበረሰብ ተወካዮች ገልጸዋል።

በውሃና በአካባቢ ብክለት ታመዋል የተባሉ አምስት ሰዎች ሁሉም በተለያየ በሽታ የታመሙ መሆናቸው የተጠቀሰ ሲሆን፤ የክልሉ ጤና ቢሮም በአካባቢው ከተለመዱ በሽታዎች ውጪ አዲስ የተከሰተ በሽታ አለመኖሩን አረጋግጧል።

በአካባቢው ፖሊ ጂሲል ኩባንያ ያስቆፈራቸው ሁለት የውሃ ጉድጓዶች ችግር እንዳሌላባቸው፤ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንና የተረፉ ግብዓቶችና ከጉድጓድ የሚወጡ ዝቃጮች አወጋገድ ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን የጥናት ቡድኑ በምልከታው መታዘቡን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

በመሆኑም ዘጋርዲያን በየካቲት 20 ቀን 2020 እትሙ ያቀረበውን ስሞታ ከእውነት የራቀና መሰረተ ቢስ በመሆኑ የማስተካከያ እርምት እንዲያደርጉ ሲል ሚኒስቴሩ ጠይቋል።