አባይ ሚዲያ ሚያዝያ 19፤2012

ከወራት በፊት ድፍን ሁለት አመት የሞላው የጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣትና የሀገራዊ ለውጥ ጅማሮ በአንድ በኩል በወቅቱ ያስተናገደው ህዝባዊ ድጋፍና ቅቡለት ተሸርሽሯል፤ ለውጡም ተቀለብሷል በሚሉ አካላት ሲተች በሌላ በኩል ከነክፍተቱ የለውጡ አመራር ሀገሪቱን ያሻግራታል በሚል ተስፋ እየተቃኘ ሀገሪቱን መምራቱን ቀጥሏል፡፡

ምናልባትም ከሁለት ወራት በፊት ሀገሪቱ ላይ ሲታይ የነበረው ፖለቲካዊ ቀውስና የሰላም መደፍረስ ወደ ከፋ ችግር እንዳያመራ ከፍተኛ ስጋት በደቀነበት ወቅት የኮቪድ-19 ወረርሺኝ ሌላ አዲስ ስጋት ፈጠረ እንጂ ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት ምን ትመስል ይሆን የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡

ወረርሺኙ ሀገራዊ ምርጫው እንዲራዘም ካስገደደ በኋላ ገዢው መንግስት ስልጣኑ እንደሚያበቃ በመጥቀስ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም የሚጠይቁ ጥቂቶች አይደሉም ከሁሉም በላይ ግን የለውጡ መንግስት በዋነኝነት የሚወቀስበት ህግ የማስከበር አቅም መላላት ዋና ተጠቃሽ ነው ይሄንን በሚመለከት የጠ/ሚ ጽ/ቤት ፕረስ ሴክረታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ምላሽ ይሰጣሉ፡፡

አቶ ንጉሱ በክልል፣ በጎጥ፣ በብሔርና በሃይማኖት ሳቢያ የነበሩትን ግጭቶች እና መከፋፈሎች ያደሩ ሂሳቦች በመሣሪያ መዝጋት አይቻልም ያሉ ሲሆን በመሳሪያ ጭጭ ማሰኘት ቢቻልም ፀጥታ ማስከበር ይቻላል እንጂ ሰላም ማረጋገጥ አይቻልም ሲሉ ገልጸዋል  ሃላፊው ፀጥታን ማስከበር እና ሰላምን ማረጋገጥ ይለያያሉ ሲሉም ይናገራሉ፡፡

ነገር ግን ተደራጅተው የዜጎችን ሰላም በሚያወኩና ወንጀል በሚፈጽሙ አካላት ላይ እርምጃ እንወስዳለን የሚሉት አቶ ንጉሱ በምዕራብ ወለጋና  አካባቢዎች ታጥቆ የሚንቀሳቀሰውን ሃይልም የክልሉ መንግሥትና የፌዴራል መንግሥት ተባብረውና ተናብበው እርምጃ ወስደውበታል በማለት ያስረዳሉ።

አሁን በቅርቡ እንዳየነውም የአካባቢውንና የቀጣናውን ሰላማዊ ሁኔታ ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል ሃላፊው  የአማራ ክልል ምዕራባዊ ቀጣናም እንደዚሁ ነው። የክልሉ መንግሥት የተለያዩ አማራጮችን አስቀምጧል። ያሉት አቶ ንጉሱ የታጠቀ ሃይል ሊኖርና የተደራጀ ሆኖ ሊሄድ የሚችለው አንድ መንግሥት ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ሃላፊው አክለውም  የፌዴራል መንግሥቱ መከላከያን ጨምሮ ካለው የታጠቀ የፀጥታ መዋቅርና ክልሎች በደረጃው ካላቸው  ውጭ ቡድን አደራጅቶና ራሱን ሰይሞ በጠራራ ፀሐይ ዘረፋ የሚያካሂድ ቡድን አማራጭ እንደተቀመጠለት ገልጸው አማራጩም በክልሉ ፀጥታ መዋቅሩ መታቀፍ የሚችለው መታቀፍ፤ በሌሎች ሥራዎች መሰማራት የሚችለው መሰማራት ነው ብለዋል፡፡

ይሄንን አልቀበልም ያለውን አካል ሕግና ሥርዓት ማስያዝ ስለሚገባ፣ አልፎ ተርፎም የፀጥታ መዋቅሩን መተናኮስ የጀመረና ጉዳትም ያደረሰ አካል ላይ እርምጃ መወሰድ ስላለበት እርምጃ ተወስዷል ይሄም ይቀጥላል ሲሉ ሃላፊው ተናግረዋል።