አባይ ሚዲያ ሚያዝያ 19፤2012

የቀድሞ የሀገሪቱ የመረጃና መረብ ደህንነት ተቋም ዋና ዳይሬክተር ሜጄር ጄነራል ተ/ብርሃን ወ/አረጋይ ከትግራይ ሚዲያ ሃውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ ያነሷቸው ነጥቦችና ያስተላለፏቸው መልዕክቶች በበዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ ቀጥሏል በተለይም ጄነራሉ የጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ የቀድሞ ቅርብ አለቃ በመሆናቸው ባለፉት አመታት ሲፈጸሙ ስለነበሩ ዘግናኝ ወንጀሎችና ስለጠ/ሚሩ አካሄድ ያደረጓቸው ገለጻዎች አስገራሚም ነበሩ፡፡

ከሁሉም በላይ ግን የጦር መኮንኑን ንግግሮች ብዙዎች እንዲቀባበሉት ያደረገው የህወሃትን የትግል አጀማመርና ከዚህ በኋላ ትግራይን ስለመገንጠል ያላቸውን አቋም ማንጸባረቃቸው ሲሆን ሜ/ጄ ተ/ብርሃን በጓዳ የሚወራውን በአደባባይ አወጡት ያሏቸውም ጥቂቶች አይደሉም ከዚሁ ጋር ተያይዞ የአረና ትግራይ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አምዶም ገ/ስላሴ ከአባይ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ የጄነራሉን ንግግር ክፉኛ አጣጥለውታል፡፡

አቶ አምዶም ሜ/ጄ ተክለብርሃን በሰልጣን ላይ እያሉ ትግራይን ከኢትዮጵያ ነጥሎ ማሰብ አይቻሉም ባሉት አንደበታቸው ከስልጣን ሲወርዱ ትግራይን እንገነጥላለን ማለታቸው ጉዳያቸው ከስልጣን ጋር መሆኑን ማሳያ ነው ሲሉ ገልጸዋል አቶ አምዶም በተጨማሪም ቀድሞው የደህንነት ሹም አማርኛን ቋንቋን ለመልመድ ያጠፋሁት ጊዜ ይቆጨኛል ማለታቸውን አንስተው ሜ/ጄ ተክለብርሃን ስልጣን ላይ ሆነው የደህንነቱን ስራ ሲመሩ አማርኛን የስራ ቋንቋቸው አድርገው ነበር ያሉ ሲሆን ቃለመጠይቃቸው ሳይቀር በአማርኛ ቋንቋ እያደረጉ ለብዝሃነት ያላቸውን አመለካከት ማጣመማቸው ተቀባይነት የለውም በማለት አስረድተዋል፡፡

ሜ/ጄ ተ/ብርሃን ወ/አረጋይ በነበራቸው ቃለመጠይቅ የታገልነው የራሳችንን ዕድል በራሳችን ለመወሰን ነው፤ አንዳንድ ሰዎች ለኢትዮጵያ ነው የታገልነው” ሲሉ እሰማለሁእንደርሱ አይደለም። የታገልነው ለኢትዮጵያ አልነበረም። ዓላማችን ኢትዮጵያ አልነበረችም ሲሉ ተደምጠው ነበር፡፡