አባይ ሚዲያ ሚያዝያ 20፤2012

ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ አገራዊው ምርጫ በጊዜው እንዲካሄድ ሲጠይቅ የነበረው ህወሓት፤ የ2012 አገራዊ ምርጫ በማንኛውም ሁኔታ መካሄድ አለበት፤ ምርጫ የማይካሄድ ከሆነ በክልል ደረጃ ምርጫ እናካሂዳለን የሚል ይዘት ያለው የአቋም መግለጫ ከአምስት ወር በፊት አስነብቦ ነበር።

ይህንኑ አቋሙን ሰሞኑን በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ በድጋሚ አስነብቧል። በዚህም የተነሳ በእርግጥ የትግራይ ክልል የራሱን ምርጫ ማካሄድ ይችላል? የሚለው የበርካቶች ጥያቄ ሆኗል የህወሓት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ነጋ ተገኝ፤ ይህ ቀደም ብሎ የነበረ አቋም መሆኑን በመግለጽ አዲስ የተወሰነ ውሳኔ መኖሩን እንደማያውቁ ይናገራሉ።

“በቅርቡ በዚህ ጉዳይ ላይ አልተነጋገርንም፤ ቀደም ብሎ የወሰድነው አቋም ነው” ያሉት አቶ ነጋ ምናልባት የሥራ አስፈፃሚው አባላት ተነጋግረው ጽሑፉ በፌስ ቡክ ላይ እንዲወጣ አድርገው እንደሆነ መረጃው እንደሌላቸው ተናግረዋል ከዚህ በፊት ግን አገሪቷ ላይ ምርጫ የማይደረግ ከሆነ እኛ እናካሂዳለን የሚል አቋም በመያዝ ምርጫውን እንዴት ማስፈፀም ይቻላል በሚለው ላይ በደንብ መወያየት እንዳለባቸው መነጋገራቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

“በዚህ ወቅት ግን በማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ በዚህ ጉዳይ አልተነጋገርንም” ያሉት አቶ ነጋ ህወሓት ምርጫው መካሄድ እንዳለበት የያዘው አቋም ከስምንት ወራት በፊት የነበረ መሆኑን ያስታውሳሉ ዶ/ር አደም ካሴ የተባሉ የአስተዳደር እና ዲሞክራሲ አማካሪ በበኩላቸው ምርጫን የማካሄድ፣ የምርጫ ሕግን የማውጣት፣ የወጣውን ደግሞ ማስተዳደር ሥልጣን ያለው የፌደራሉ መንግሥቱና ምርጫ ቦርድ ነው ሲሉ ይናገራሉ።

ከዚያ ውጪ የህወሓት አመራሮች ሕጉን ተከትለው ካልተቃወሙ በስተቀር በራሳቸው ዝም ብሎ መሄድ ስልጣኑም የላቸውም ይላሉ የሕግ አማካሪው አቶ ኤፍሬም ደግሞ ” አገር አቀፍ ምርጫ ባልተደረገበት በክልል ምርጫ እንደርጋለን ማለት፣ የፌደራል ዲሞክራሲያዊ ተቋም ባልተሳተፈበት፣ ባልታዘበበት ምርጫ ማድረግ የምርጫውን ሕጋዊነት፣ ነፃና ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ ይጥለዋል” በማለትም ክልሉን የሚያስተዳድረው ፓርቲ ህወሓት፤ ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል ያብራራሉ።

“ምርጫ ሲባል ዝም ብሎ አንድ ቀን ሄዶ መምረጥ አይደለም” የሚሉት ዶ/ር አደም በበኩላቸው “በቅድሚያ የምርጫ ወረዳዎች መወሰን አለባቸው። ያለውን እንኳ ይጠቀማሉ ቢባል ያም እንደገና መወሰን አለበት። ከዚያም ሲያልፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች መመዝገብ ያስፈልጋቸዋል” በማለት ሂደቱን ያብራራሉ።

አቶ ኤፍሬም በተጨማሪም ምርጫ ቦርድ አገራዊ ምርጫውን ሲያራዝም አገሪቱ በኮቪድ-19 ስጋት ውስጥ ስላለች ነው በማለት “አሁን ባለንበት ሁኔታ የተለያዩ የሲቪልና ፖለቲካዊ መብቶች ይገደባሉ” ይላሉ እነዚህ መብቶች መካከል ደግሞ የመመረጥና የመምረጥ መብት እንደሚገኝበት በመግለጽ ይህ ጉዳይ ሕገ መንግሥቱ ላይ የሰፈረ፣ ምርጫ ቦርድም በሕገ መንግሥቱ መነሻነት ያንን ውሳኔ ማሳለፉን ይገልፃሉ “ስለዚህ ሁኔታዎች ተሻሽለው ወደ መደበኛው ሕይወት እስክንመለስ ድረስ ስለምርጫ የምናወራበት ሕገ መንግሥታዊ መሰረት ያለን አይመስለኝም” ይላሉ።