አባይ ሚዲያ ሚያዝያ 20፤2012

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለም ላይ በከፍተኛ ደረጃ መሰራጨት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ካስከተላቸው ቀውሶች መካከል ከፍተኛ ስጋት እያጫረ የሚገኘው በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ስደተኞች ጉዳይ ነው የሀገር ውስጥ መፈናቀል መቆጣጠሪያ ማዕከል /አይ.ዲ.ኤም.ሲ/ በሪፖርቱ በዓለም ዙሪያ 50 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሰዎች በግጭት ወይም በአደጋ ምክንያት በሀገር ውስጥ መፈናቀላቸውን አስታውቋል።

ኢትዮጵያ ዉስጥ ደግሞ የሐገር ዉስጥ ተፈናቃዩ ቁጥር ባይታወቅም 760 ሺሕ ስደተኞች በየመጠለያ ጣቢያዉ ሰፍረዋል አብዛኞቹ ስደተኞች የደቡብ ሱዳን፤ የሶማሊያና የኤርትራ ዜጎች ሲሆኑ ስደተኞቹ የሚኖሩት ተፋፍገዉ ነዉ ኮቪድ 19ን የመሰለዉን አደገኛ ተሕዋሲ የሚከላከሉበት የንፅሕና መገልገያ፣ ጭምብልም ሆነ ጓንት አያገኙም ስደተኛዉ በተሕዋሲዉ መለከፍ አለመለከፉ የሚመረመርበት መሳሪያም የለም።

በየዓረብ ሀገራቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መመለስ እንደሚፈልጉ በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርቡ የቆዩ ቢሆንም እስካሁንም ድረስ መንግስት ምላሽ እንዳልሰጣቸው እየገለፁ ነው የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ እነሱን ለመመለስ ሀገራት በወረርሽኙ ስጋት ምክንያት አለም አቀፍ በረራዎችን በማገዳቸው ተግዳሮት ሆኖብኛል ቢልም አሁን ደግሞ ዜጎቹን በተመለከተ ኮሚቴ አዋቅሬ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራሁ ነው ብሏል፡፡

የሀገር ውስጥ መፈናቀል መቆጣጠሪያ ማዕከል በዓመታዊ ሪፖርቱ እንዳስጠነቀቀው፥ የኮቪድ -19 ወረርሽኝ ቀድሞውኑ ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑና በሀገር ውስጥ ለተፈናቀሉ ሚሊዮኖች ተጨማሪ አደጋዎችን ሊያስከትል የሚችል አዲስ ስጋት ነው ብሏል ከ45 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ሰዎች በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ሲሆን አምስት ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ በተፈጥሮ አደጋዎች መፈናቀላቸውን ማዕከሉ አስታውቋል።

እነዚህ ተፈናቃዮች ንጽህና በጎደላቸው ድንገተኛ መጠለያዎች፣ መደበኛ ባልሆኑ ሰፈሮች እና የከተማ መንደሮች የሚኖሩ በመሆናቸው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል አስቸጋሪ ነው መንግስታት ተፈናቃዮች በዚህ ከባድ የወረርሽኝ ወቅት የጤና እንክብካቤ እንዲያገኙ ማድረግ እንዲሁም ረዘም ላለ ጊዜ የመፈናቀላቸውን ምክንያቶች ለመቅረፍ እንዲሰሩ ተቋሙ ጥሪ አቅርቧል።

የተባበሩት መንግስታት የጤና ድርጅት (WHO) ችግሩ ለጠናባቸዉ ስደተኞች የኮቪድ 19 መከላከያና መመርመሪያ መሳሪያዎችን ለመስጠት እየጣረ ቢሆንም ዩናይትድ ስቴትስ ለድርጅቱ የምትሰጠዉን መዋጮና ድጎማ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በማቋረጣቸዉ ወትሮም እጅግ አናሳዉን የድርጅቱን ርዳታ በእጅጉ ይቀንሰዋል።

በ30 ሐገራት የሚኖሩ ስደተኞችንና ተፈናቃዮችን የሚረዳዉ የኖርዌ የስደተኞች መርጃ ምክር ቤት ኃላፊ የን ኤግላንድ እንደሚሉት ኮቪድ 19 ስደተኞችና ስደተኞች በሰፈሩባቸዉ ሐገራት እንዳይሰራጭ ሐብታሞቹ ሐገራት ቢረዱ ርዳታዉ የሚጠቅመዉ ለራሳቸዉም ጭምር ነዉ «ምክንያቱም ወረርሺኙ ከእነሱ ጠፍቶ ወደ ሌላ ሀገራት ቢሰራጭ ተመልሶ መግባቱ አይቀርም።» ባይናቸዉ ኮቪድ 19  የስደተኛ መጠለያ ጣቢዎችን ከወረረ ለስደተኛዉ ተጨማሪ ፈተና፣ ስደተኛዉን ለሚያስተናግደዉ ማሕበረሰብም የጥላቻ መቀስቀሻም የበሽታ ዑደት መሠረትም  ነዉ የሚሆነዉ የሚሉት ደግሞ የህክምና ባለሙያዎች ናቸው።