አባይ ሚዲያ ሚያዝያ 21፤2012

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ /አብን/ ዛሬ ባወጣው መግለጫ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአዲስ ማህበራዊ ውል ድርድር የሚያስፈልበትና የኢፌዴሪ ሕገ መንግስትን የማሻሻያው ጊዜ አሁን ነው ይላል፡፡

ሀገሪቱ አሁን ባለችበት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኢፌዴሪ ሕገ መንግስትም ሆነ በሌሎች የአገሪቱ ሕጎች ምርጫ ስለማራዘምም ሆነ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የአስፈጻሚውን ስልጣን ማራዘም የሚቻልበት ግልጽ ድንጋጌ እንደሌለ የገለጸው አብን ሁኔታው የብሔራዊ የአንድነትና ጊዜያዊ መንግስት የማቋቋም ብሄራዊ ድርድር ግዴታ መሆኑን ይጠቁማል፡፡

ንቅናቄው መሻሻልና መቀየር ያለባቸው የሕገ መንግስቱ አንቀጽ ናቸው ብሎ ያስጠናቸውና የለያቸው ነጥቦችንም ዘርዝሯል ከህገ መንግስቱ መግቢያ ጀምሮ «እኛ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች» የሚለው ገለጻ ከልዩነት ይልቅ አንድነትን ሊያጎላ በሚችል «የኢትዮጵያ ሕዝብ» በሚል አገላለጽ መተካት አለበት ያለው አብን የኢትዮጵያ ሰንደቀላማ ላይ ምንም አይነት አርማ ሊቀመጥበት አይገባም ብሏል።

በተጨማሪም አማርኛ የፌደራል መንግስቱ የስራ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ መሆን መቻል እንዳለበት የጠየቀው መግለጫው  አማርኛ ብሔራዊ ቋንቋ ባለመሆኑ የተነሳና የፌደራል መንግስቱ የስራ ቋንቋ ብቻ በሚል በመጠቀሱ የተነሳ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ላይ ተፅዕኖ እያደረሰባቸው እንደሚገኝ ያስረዳል፡፡

ሌላው አብን ቢቀር ያለው አንቀጽ 39 የመገንጠልን ጽንሰ ሃሳብ ሲሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ሊሰጠው ይገባል፤ ነገር ግን የመገንጠል መብት የአገሪቱን ሉዓላዊ አንድነት ለአደጋ ስለሚያጋልጥ አያስፈልግም ብሏል፡፡

አብን የክልሎችን አወቃቀር በተመከለተ ያነሳው ዋናው ጥያቄ ደግሞ አንድን ክልል ለአንድ ብሔር በሚል በአንቀጽ 47 መሠረት የተቋቋሙ ክልሎች መፍረስ አለባቸው ያለ ሲሆን አሁን ያለው የክልሎች አወቃቀር ታሪካዊ ግዛቶችን የከፋፈለና የአማራን ሕዝብ የማንነት፣ የቋንቋ፣ የባኅል፣ የሕይዎት፣ የኢኮኖሚ ወዘተ. መብቶች የማያስከብር ነው ሲል አብራርተቷል።

ለዚህም በምሳሌነት ያነሳው መተከል የሚባለውን የቤንሻንጉል ክልል ግዛት እንዲሁም  አማራ የሚበዛበት ነው ያለውን  የሃረሪ ክልልን ሲሆን የክልል ባለቤትነትን ለአንድ ወይም ለተወሰነ ቡድን መስጠት ነው ያለ ሲሆን እንዲህ አይነት ሁኔታዎችን ለማስቀረት ክልሎች መፍረሳቸው የግድ ነው በማለት አስረድቷል።

በተጨማሪም ንቅናቄው ድሬዳዋ  በአሁኑ ሰዓት የሶማሌና የኦሮሞ ፖለቲከኞች እርስ በእርስ የሚጓተቱባት ከተማ ስለሆነች፣ ድሬደዋ ከተማ ከአዲስ አበባ ጋር አብራ በሕገ መንግስት የፌደራል መንግስት ዋና መቀመጫ መሆን እንዳለባት አስምሯል፡፡

ሌላው በተለያየ አረዳድ መነታረኪያ ሆኖ የቀጠለውን የኦሮምያ ክልል ልዩ ጥቅም ጉዳይ መግለጫው አንቀጹ ሊወጣ ይገባል ያለ ሲሆን የፌደራል መንግስት መቀመጫ ከተሞች በዙሪያቸው ካለው ሕዝብ ጋር ጥቅምና ግዴታን እየተጋሩ ሊቀጥሉ ይገባል እንጂ አንድን ሕዝብ ነጥሎ ልዩ ጥቅሙ ይጠበቅለት ማለት እንደአገር ማሰብን የሚያስቆም ነው ሲል ያትታል፡፡

የፓርቲው መግለጫ ከተጠቀሱት በተጨማሪም የምርጫ ስርአቱን በተመለከተ፤ የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላትን አወካከል እንዲሁም የፌደራል መንግስት ያለአግባብ በክልሎች የሚገባበት ሁኔታ እንዳለ በመጠቅስ አቋሙን ግልጽ አድርጓል፡፡