አባይ ሚዲያ ሚያዝያ 21፤2012

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መበተን: የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ: ህገ መንግስት ማሻሻልና የህገ መንግስት ትርጓሜ መጠየቅ መንግስትና የተፎካካሪ ፓርቲዎች ፊት ለፊት ገጥመው የሚሟገቱባቸው አንኳር ነጥቦች ሆነው ተለይተዋል ተወያዮቹ  ቀጣዩ ምርጫ ሊካሄድባቸው የሚችሉትን መጻኢ ሁኔታዎች፣ እንዲሁም ከምርጫው መራዘም ጋራ ተያይዞ ሕገ መንግሥቱ ግልጽ ምላሽ የማይሰጥባቸውን ሁኔታዎች በጋራ መግባባት መመለስ የሚቻልበትን ሁኔታ መነጋገር ተገደዋል፡፡

ሆኖም ይህ ውይይት ቀጣይነት እንዲኖረው ስለመታሰቡ አባይ ሚዲያ ማረጋገጥ ባይችልም በዛሬው ስብሳብ ግን ስብሰባ አራተኛው አማራጭ ማለትም የህገ መንግስት ትርጓሜ መጠየቅ ለምን ተመራጭ እንደሆነ ለማሳወቅ የታሰበ እንደሚመስል የውስጥ ምንጮች ይጠቁማሉ ህገ መንግስቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ህገ መንግስቱን የመተርጎም ስልጣን ቢሰጠውም በህገ መንግስቱ መሰረት ሀገ መንግስቱን መተርጎም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄውን የሚያቀርበው ጉባኤ የመንግስትን ስልጣን ለማራዘም የሚፈቅድ አንቀፅ ማግኘት አዳጋች እንደሚሆንበት እየተነገረ ይገኛል፡፡

ያም አለ ይህ በዛሬው ስብሳባ ላይ የእነ አቶ ልደቱ አያሌው ኢዴፓ፤ የእነ ኢንጅነር ይልቃል ኢሃን እንዲሁም አብን እንዳልተሳተፉ ከፓርቲዎቹ አማራር አባላት ለማወቅ ችለናል ይህ በእንዲህ እንዳለ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመጪው ነሐሴ ወር ሊካሄድ ታስቦ የነበረውን አጠቃላይ ምርጫ በተመለከተ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ መክሮ ውሳኔ ለማሳለፍ፣ ነገ ሐሙስ ሚያዚያ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚሰበሰብ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 60 ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርጫ ለማካሄድ ሲባል በሥራ ላይ ያለውን ፓርላማ የሥልጣን ዘመን ከማብቃቱ በፊት እንዲበተን የውሳኔ ሐሳብ በማቅረብ፣ በምክር ቤቱ በሚሰጠው ውሳኔ ምክር ቤቱ የሚበተንበት ሥነ ሥርዓት ተደንግጓል አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች ይኼንን አንቀጽ በመጠቀም አሁን ያጋጠመውን ሁኔታ ማለፍ እንደሚቻል ቢገልጹም፣ ሌሎች የሕግ ባለሙያዎች በበኩላቸው ይህ አንቀጽ የተቀመጠው በምርጫ የተመሠረተ መንግሥት የሥልጣን ዘመኑ ጅማሮ ወይም መካከል ላይ ቅቡልነቱን ቢያጣ አዲስ ምርጫ ለማካሄድ እንጂ፣ የምርጫ ጊዜን ለማራዘም እንዳልሆነ ይከራከራሉ።

የተለየ ሐሳብ የሚያንፀባርቁ የሕግ ባለሙያዎች በበኩላቸው አሁን በተፈጠረው የቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመጠናቀቁ አስቀድሞ፣ ለተጨማሪ ስድስት ወራት እንዲራዘም በማድረግ ምርጫው እንዲገፋ ማድረግ እንደሚቻል ይገልጻሉ እነዚህ ባለሙያዎች ይህንን አማራጭ የሚያነሱት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር ማድረግ፣ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት (ከአራት አንቀጾች ውጪ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እስኪያበቃ ድረስ ተፈጻሚነት እንዳይኖረው የሚያደርግ ውጤትን የሚያስከትል በመሆኑ ነው ነገር ግን ይህ ሐሳብ በሌሎች የሕግ ባለሙያዎች ተቀባይነት የለውም ምክንያቱ ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንድ የገጠመን እክል ለማለፍ ጥቅም ላይ የሚውል እንጂ፣ ምርጫን ለማራዘም የሚሠራ አለመሆኑንና ሥልጣንን ያላግባብ እንደ መጠቀም እንደሚቆጠር ይገልጻሉ።