አባይ ሚዲያ ሚያዝያ 24፤2012

የኢዜማ፣ የኦፌኮና አረና ፓርቲ አመራሮች አገሪቱ ከገባችበት አጣብቂኝ ችግር ውስጥ ለመታደግ መንግሥት በህግ ባለሙያዎች ጥናት በማስጠናት ያቀረባቸው አራት አማራጮች የፖለቲካ መሪዎቹ ህግን መሰረት ያደረጉ መሆኑን አስታውቀዋል የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ  «እኛ ከቀረቡት አማራጮች ውስጥ ህገመንግሥት ማሻሻልና የህገመንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ የሚሉት አማራጮች በጣምራ ቢታዩ የሚል ሃሳብ ሰጥተናል» ያሉ ሲሆን ለዚህ ደግሞ በዋናነት ከዚህ ቀደም በነበረው የፖለቲካ ታሪክ ህዝቡንም ሆነ ፓርቲዎችን ውዝግብ ውስጥ የከተቱ በርካታ የህግመንግሥት አንቀፆች በመኖራቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የቀረቡት አማራጮች የህገመንግሥታዊ ሂደቱን የማያደናቅፉ፤ የአገር አንድነትን አደጋ ላይ የማይጥሉና ከህገመንግሥት ያልወጡ መሆናቸውን በግላቸው መገንዘባቸውን አመልክተዋል በቀጣይ በሚኖረን ውይይት የሚዳብር መሆኑ ደግሞ ፓርቲዎቹ አሳታፊ የሆነ ውሳኔ እንዲወስኑ እድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል «በእኛ በኩል ከህግ አማካሪዎቻችን ጋር ይህ አማራጭ ሊያስኬደን እንደምንችል እየተወያየን ነው» ብለዋል፡፡

የኦፌኮ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና በበኩላቸው፤ ጉዳዩ ገዢውን ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ሁሉም የፖለቲካ ተዋናዮች የሚመለከት ወሳኝ ጉዳይ እንደመሆኑ ከውይይት በፊት ፓርቲዎቹ በተናጠል ሰነዱ እንዲደርሳቸውና ውይይት እንዲያደርጉበት መደረግ እንደነበረበት አመልክተዋል «ይህ ባለመሆኑ ግን ሁሉም እንደመሰለው የግሉ አስተያየት ለመስጠት ተገዷል» በማለት ገልፀዋል፡፡

«ምርጫው መረዛሙ ካልቀረ መነጋገሩ ለእኔ ጥሩ ነው፡ ነገር ግን መሰረታዊ ስህተቱ ብዬ የማምነው የህገመንግሥት አንቀጽ ወደ መቀየር ለመሄድ መሞከሩ ነው» ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ከዚህ ይልቅ ፖለቲካዊ አማራጮችን መከተል የተሻለ እንደነበረ አንስተዋል ለዚህ ደግሞ በምክንያትነት አገሪቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ፖለቲካዊ ችግር ውስጥ የወደቀች በመሆኑና ይህንን ለመፍታት በድርድር የጋራ መንግሥት ማቋቋም አለመቻሉ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ፓርቲያቸው ይህንን ጉዳይ በሚመለከት በተደጋጋሚ ሃሳብ ሲያቀርብ መቆየቱንም ፕ/ር መረራ አስታውሰዋል፡፡

የአረና ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጎይቶም ፀጋዬ ደግሞ በውይይት መድረኩ የተለያዩ ገንቢ ሃሳቦች መሰንዘራቸውን አንስተው ህወሃትን ወክለው ከተገኙ ተሳታፊዎች አማራጮቹ አካታች እንዳልሆኑ ተደርጎ የቀረበበት መንገድ ስህተት እንደነበር ተናግረዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉትም የህወሃት አመራሮች በመጀመሪያ ራሳቸውን መፈተሽን ለሚመሩት ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ምህዳር መፍጠር እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል አቶ ጎይቶም « ህወሃቶች እነሱ በመጀመሪያ ብልፅግናን የሚጠይቁት ነገር ትግራይ ውስጥ ሊያደርጉት ይገባል:: እነሱ የቀረቡትን አማራጮች አካታች አይደለም ከማለታቸው በፊት እነሱ ለትግራይ ህዝብ አካታች መሆናቸውን ራሳቸውን ሊጠይቁ ይገባል» ብለዋል፡፡