አባይ ሚዲያ ሚያዝያ 24፤2012

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በሃገራችን መከሰቱን ተከትሎ ነሃሴ 23 ሊካሄድ የታሰበው ሃገራዊ ምርጫ በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ መሰረት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲራዘም መወሰኑን ተከትሎ  በሃገሪቷ የሚገኙ  የተለያዩ  የፖለቲካ ፓርቲዎች መከራከሪያዎችን እያነሱ መንግስት ይበጃሉ ያላቸውን አራት አማራጮች መሞገታቸውን ቀጥለዋል፡:፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ከአባይ ሚዲያ ጋር ቆይታ ያደረጉት የህብር ኢትዮጵያ ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ የብልጽግና ፓርቲ ያቀረበውን የምርጫ አማራጭ እንደማይደግፉ ገልጸዋል አቶ ግርማ እንዳሉት መቶ ሰባቱ ፓርቲዎች መመስረት ስለሚገባው የሽግግር መንግስት በጋራ ተወያይተው ሰባት አጀንዳዎችን ካጸደቁና ለተግባራዊነቱም እየሰሩ በሚገኙበት ወቅት መንግስት በመሃል ተነስቶ አራት አማራጮችን ማቅረቡ ቅቡልነት የለውም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

አቶ ግርማ  ከ100 በላይ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ መኖራቸው በራሱ ከ100 በላይ የፖለቲካ ፕሮግራም አላቸው ማለት እንዳልሆነም ገልጸዋል ለሽግግር መንግስትነት ፓርቲዎች ሲወከሉ በአላማቸው በቡድን በቡድን  ተለይተው ወኪላቸውን የሚያቀርቡበት ሁኔታም መፍጠር ይቻላል ያሉት አቶ ግርማ ድርጅታቸው ህብር ኢትዮጵያም በጠቅላይ ሚኒስተር ቢሮ በነበረው ስብሰባ እንዳልተጋበዘ ነግረውናል፡፡

ህብር አትዮጵያ ፣ኢዴፓና ኢሃን በአብሮነት ማእቀፍ የሽግግር መንግስት መመስረት ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ሁኔታ የመውጫ መንገድ ነው ብለው እንደሚያምኑም አሳውቀዋል ሊቀመንበሩ 547 የፓርላማ መቀመጫ ላለው መንግስት 107 ፓርቲዎች መኖራቸው ችግር አይሆንም ሲሉም ሃሳባቸውን ገልጸዋል፡፡