አባይ ሚዲያ ሚያዝያ 25፤2012

መንግስት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫ ማካሄድ ባለመቻሉ አራት የቢሆን አማራጮችን ማቅረቡን ተከትሎ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና የህግ አካላት አስተያየታቸውን ሲሰጡ ሰንብተዋል የነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኑር ወለላ የምርጫው መራዘም ትክክል መሆኑን ገልፀው ፓርቲያቸው ከተመላከቱት ቢሆኖች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅና ምክር ቤቱን መበተን የሚሉት አማራጭ ሐሳቦች ውስንነት ያሉባቸው በመሆናቸው ‘‘ለችግሩ ሁነኛ መውጫ መንገድ አይሆኑም’’ ብሎ እንደሚያምን ተናግረዋል፡፡

ምንም ዓይነት የሐሳብ መቀራረብ የማይታይባቸውና በራሳቸው ጫፎች ላይ የቆሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ሳይኖራቸው የሽግግር መንግሥት መሥርተው ካለው ወረርሽኝ አንጻር ሀገር ለመምራት በእጅጉ ከባድ እንደሚሆንም ስጋታቸውን ገልጸዋል ከችግሩ ለመውጣት የሚቻለው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 58 (3) ላይ የቀረበውን ድንጋጌ በማሻሻል እንደሆነም አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የምርጫው መራዘም በሀገር ጥቅምና በሕገ መንግሥቱ መሠረት እንዲሠራ የግድ እንደሚል ተናግረዋል መንግሥት ካቀረባቸው አራት ሐሳቦች አንፃር በሕገ መንግሥቱ የሚሻሻሉ አንቀፆች በሰላማዊ አግባብ እስኪፈቱ ባለው ማዕቀፍ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ሀገሪቷን እንደሀገር ለማስቀጠል የፖለቲካ ፓርቲዎች በሐሳብ ስለተቃረኑ የሚያሰጋ ሊሆን አይገባም፤ የፖለቲካ ሥራ ላይ አስተዳደራዊ ጫና ቢኖርም ሀገር በሕዝቦች ስምምነት የቆመች መሆኗን መረዳት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል የቀረቡት አማራጮች የሀገር ውስጥ ማሻሻያዎች ለማድረግ አለማስቻልና ከሀገር ውጭ ከሚኖር ግንኙነት እና ተፅዕኖ አንጻር ለመቋቋም የሚያስችሉ አለመሆናቸው ነጻ የፓርቲዎች እንቅስቃሴን በመፍቀድ በፖለቲካዊ ስምምነት መፍታት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ ‘‘ስልጣን ላይ ያለ አካል በዚህ ሂዱ ብሎ መወሰን ይችላል’’ ብለዋል መንግሥት ይህን በመረዳት ለሀገር እና ለሕዝብ የሚበጅ ጥሩ አማራጭ እንደሚያመጣ ተስፋ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥ ሆኖ የምርጫው መራዘም ፓርቲዎች ጥምረት እንዲፈጥሩ፣ እንዲዋሐዱ እና ለሕዝብ የሚበጅ አጀንዳቸውንም እንዲያጠናክሩት እና እንዲከልሱት ዕድል ሊፈጥር እንደሚችልም አንስተዋል፡፡

የአብን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጣሂር ሙሐመድ ደግሞ ‘‘አሁን ባለው የሕግ ማዕቀፍ ምርጫ አራዝሞና ሕጋዊ መንግሥት ሆኖ መቆየት አይቻልም፡፡ ሁለት ምርጫ አለ፤ ‘በፖለቲካ ድርድር አማካኝነት በባላአደራ የሽግግር መንግሥት ወይስ ፓርላማው ተበትኖ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የኃይል ገደብ መቀጠል አለበት?’ የሚል ስምምነት ያስፈልጋል’’ ነው ያሉት መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ እስከ ዛሬ ድረስ የ51 ሀገራትና የክልሎች ምርጫ መራዘሙን ታውቋል፡፡