አባይ ሚዲያ ሚያዝያ 25፤2012

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በሃገራችን መከሰቱን ተከትሎ በርካታ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶች በመከሰታቸው በርካታ ስጋቶች የተደቀኑ ቢሆንም በዋናነት ግን እነዚህን ቀውሶች ተከትሎ የሚመጣው ፖለቲካዊ ጣጣ  ገና ካሁኑ ብዙ እያነጋገረ እንደሚገኝ ሰሞኑን ተስተውሏል በተለይ ደግሞ ብልጽግና ፓርቲ ሰሞኑን  ያስቀመጣቸው ምርጫን የማራዘሚያ አራት የመፍትሄ አቅጣጫዎችና በምርጫ ቦርድ ጥያቄ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ የተወሰነው ሃገራዊ ምርጫ ትልቅ ቦታ የተሰጣቸው ሰሞንኛ ጉዳዮች ሆነው ሰንብተዋል፡፡

ይህንንም ተከትሎ ከኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ  ጋር ቆይታ ያደረጉት አቶ ልደቱ አያሌውና አቶ ጀዋር መሃመድ  ህገ መንግስቱ ስልጣንን ለማራዘም የሚያስችል ምንም አይነት ክፍተት ስለሌለው ማሻሻል እንደማያስፈልገውና፤አማራጩም ፖለቲካዊ ውሳኔ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል የኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌው አሁን ላይ ህግ የማይፈታቸው በርካታ ቅራኔዎች በሃገራችን ስለተከሰቱ ከህግ ያለፈ መፍትሄ የሚያስፈልጋቸው ችግሮች ገጥመውናል፤ ስለዚህ ለገጠመን ችግር መፍትሔውን ህገ መንግስት ላይ መፈለግ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአስቸኳይ አዋጅ አውጆ የስልጣን ዘመንን ማራዘም አይቻልም ፤ነገር ግን ህገ መንግስት አሻሽሎ ስልጣን ማራዘም ይቻል ይሆናል ይህ ደግሞ ህገ ወጥነትና አምባገነንነትን የሚያሳይ ተግባር ነው ሲሉ አቶ ልደቱ ያስረዳሉ አቶ ልደቱ አያይዘውም ብልጽግና ፓርቲ በቅርቡ የጠራው የተቃዋሚ ፓርቲዎች የጋራ ውይይት የታይታ መሆኑን ገልጸው ፤ይህ ሁሉንም የሚመለከት ጉዳይ ስለሆነ አንዱ ጋባዥ ሌላው ተጋባዥ የሚሆንበት ምክንያት የለም ፤ ስለዚህም መንግስት ለህዝብ ግንኙነት የተጠቀመበት መሆኑን እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡

አሁን ያለው መንግስት ከአማካኝ ደረጃ በታች የሆነ ደካማ መንግስት ስለሆነ የአብረን እንስራ ጥያቄዎችን ስልጣን እንደመጋራት ጥያቄ ሳይሆን እዳን እንደመጋራት ሊወስደው እንደሚገባም ገልጸዋል ብልጽግና ፓርቲ ይህንን አጋጣሚ ተጠቅሞ በጋራ የምንወስንበትን እድል የማያመቻች ከሆነ ከመስከረም 30 በኋላ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ እኩል ስለሚሆን ማንም ውሳኔ አስተላላፊ እንደማይሆን አቶ ልደቱ ይናገራሉ፡፡

አቶ ልደቱ አክለውም አሁን ላይ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ መንግስት በፍጥነትና በችኮላ ከወሰነ ለሚፈጠረው ችግር ሁሉ ተጠያቂ ይሆናል ሲሉም አሳስበዋል በዚሁ መድረክ ላይ የተገኙት አቶ ጀዋር መሃመድ ደግሞ ህገ መንግስቱ ስልጣንን ለማራዘም የሚያስችል ምንም አይነት ክፍተት የለውም ስለዚህ ህገ መንግስቱን ማሻሻል የማይታሰበ ነው ይላሉ፡፡

ይህ ከሆነ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቀራርበው እስከመጪው ምርጫ የሚቆይ የፖለቲካ ስምምነት ወይም ቃል ኪዳን መፈጸም ብቸኛው መፍትሄ መሆኑን ያስረዳሉ አቶ ጀዋር መንግስት የአብረን እንስራ ጥያቄውን አይቀበለውም የሚል እምነት የለኝም ፤አልቀበለውም ካለ ግን ሃገሪቷ ከመስከረም 30 በፊት ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ልትገባ ትችላለች ሲሉ አሳስበዋል፡፡