አባይ ሚዲያ ሚያዝያ 27፤2012

በብዙዎች ዘንድ መከራከሪያ ሆኖ የሰነበተውና የ 2012 ምርጫን ማካሄድ ባለመቻሉ መፍትሔ ይሆናሉ ብሎ መንግስት ይዟቸው ብቅ ያለው አራት የአማራጭ ሀሳቦች ብዙ ፖለቲከኞችን ቃላት ሲያወራውር ከርሟል በትላንትናው ዕለት ደግሞ ሰባት የፖለቲካ ድርጅቶች የጋራ መግለጫ አውጥተዋል፡፡

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር፣ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ፣ የአገው ብሔራዊ ሸንጎ፣ የሞቻ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ አረና ትግራይ ለሉዓላዊነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ እንዲሁም ከፋ አረንጓዴ ፓርቲ ”መንግሥት ያቀረባቸውን አማራጮች ገምግመን የራሳችንን አቋም ይዘናል” ብለዋል።

ፓርቲዎቹ እንዳሉት ከሆነ መንግስት ያቀረባቸው አማራጮች አዋጪ ባለመሆናቸው መንግስት ምርጫው እንዴትና መቼ መካሄድ አለበት በሚለው ላይ ብቻ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ድርድር ማድረግ አለበት በፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ሊቀመንበርነት የሚመራውና የመድረክ አባል የሆነው የኢትዮጵያ ሶሻሊስት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ይህንን የሰባቱን ፓርቲዎች አቋም እንደሚቃወም አስታውቋል፡፡

በዚሁ ጉዳይ ላይ ከአባይ ሚዲያ ጋር ቆይታ ያደረጉት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ መንግስት አማራጭ ብሎ ለውይይት ያቀረበውና ውሳኔ ያስተላለፈበት የህገ  መንግስት ትርጓሜ መጠየቅ ምን ጠንካራ ጎንና ደካማ ጎን አለው የሚለውን ሳናይ መቃወም ተገቢ ባለመሆኑ የፓርቲዎቹን አቋም አንደግፍም ብለዋል አሁን ከመንግስት ጋር እንደራደር የሚሉት ፓርቲዎች ተደራድረው መግባባት የሚችሉ ናቸው ወይ የሚለውም ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ፕሮፌሰር በየነ አንስተዋል፡፡