አባይ ሚዲያ ሚያዝያ 28፤2012

የኢትዮጵያ መንግሥት የኮቪድ-19ን ለመከላከል ያስተላለፋቸው ገደቦችና ለአምስት ወራት የደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመናገር ነፃነትን ለመገደብ እየተጠቀመበት ነው ሲል የሂዩማን ራይትስ ዎች ተቸ ድርጅቱ በመግለጫው ባለፈው ወር ጠበቃ ኤልሳቤጥ ከበደና ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ አስተያየት በመስጠታቸው መታሰራቸውን ጠቀሷል።

ሪፖርቱ እንዳለው ኮሮናቫይረስ በአገሪቱ እንዳይስፋፋ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋዜጠኞችንና መንግሥትን የሚተቹትን ለማሰር እየዋለ ነው “ስለቫይረሱ የሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎች ስጋት ቢሆኑም የመናገር ነፃነትን ለመገደብ ግን ሰበብ ሊሆኑ አይገባም” ያሉት የድርጅቱ የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ላይቲቲያ ባደር፣ መንግሥት ያየሰው ሽመልስ ላይ የከፈተውን ክስ ውድቅ ማድረግ፣ ኤልሳቤጥ ከበደንም ከእስር መልቀቅ አለበት እንዲሁም ሰዎች በሰላማዊ መንገድ ሃሳባቸውን ስለገለፁ ብቻ ማሰር ማቆም ይገባዋል ሲሉ ተናግረዋል።

ከወራት በፊት ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ በግል የማህበራዊ ትስስር ገጹ ላይ መንግሥት በኮቪድ-19 ምክንያት ለሚሞቱ ሰዎች 200 ሺህ ጉድጓዶች እንዲቆፈሩ አዝዟል ሲል ጽፏል በወቅቱ መንግሥት መረጃው ስህተት ነው ሲል አስተባብሏል በኋላም የአዲስ አበባ ፖሊስ ሐሰተኛ መረጃ በማሰራጨት በሚል ካሰረው በኋላ ለሶስት ሳምንት ክስ ሳይመሰርት እንዳቆየው የገለፀው መግለጫው፣ በኋላም ላይ የፌደራል ፍርድ ቤት ለጋዜጠኛ ያየሰው የዋስትና መብቱን አስጠብቆለት ሊለቀቅ መቻሉን መግለጫው አክሎ አስፍሯል።

በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር በጎ ፈቃደኛ ጠበቃ የሆነችው ኤልሳቤጥ በሐረሪ ክልላዊ መንግሥት በቁጥጥር ስር መዋሏን ድርጅቱ ጨምሮ አስታውቋል ድርጅቱ አገኘሁት ባለው መረጃ ኤልሳቤጥ ግጭት የሚያነሳሳ ሀሰተኛ መረጃ በፌስ ቡክ በማሰራጨት ተወንጅላ እስካሁን ክስ አልተመሰረተባትም ብሏል ግለሰቧ በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል ያለቻቸውን ሰዎች በስም ጠቅሳ በፌስቡክ ገጿ ላይ መፃፏ ተገልጿል።

የክልሉ ባለሰልጣናት በቫይሱ ተይዘዋል ተብለው በስምና በብሔር የተጠቀሱ ሰዎችን እንዲሁም ከእነሱ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሰዎች በአጠቃላይ ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ መደረጉን ገልፀዋል በወቅቱ በግለሰቧ የተፃፈው መረጃ ተሰርዞ ማስተካከያ ተደርጎበታል ሂዩማን ራይትስ ዎች እንዲህ አይነት መረጃዎች ግለሰቦችን ደህንነት የሚጋፋ መሆኑን በመጠቀስ የግለሰቦችን የህክምና መረጃ ይፋ ማድረግ ለማግለልና መድልዖ ያጋልጣል ሲል አስፍሯል ነገር ግን እንዲህ አይነት ድርጊቶች በወንጀል መታየት የለባቸውም ሲል በመግለጫው ላይ አስቀምጧል በአጠቃላይም ድርጅቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት የሚደርሱ ጥሰቶችን ለመከላከል ገለልተኛ አካል ምልከታ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስቧል።